የክብር
ዶክትሬትና የጨዋታ ሜዳው!
መከበር
የሚገባውን ሰው ማክበር ለተከበረው ግለሰሰብ ብቻ ሳይሆን ራስንም ጭምር ያስከብራል፡፡ በግለሰብ ደረጃ የሰው ልጆችን
ሀብት፣ሃይማኖት፣አስተሳሰብ፣ዕድሜ፣ዘር ሳይለዩ ማክበር ተገቢ ከመሆኑ ባሻገር የህሊና እርካታም ይሰጣል፡፡ የማንኛውም ሃይማኖት
አስትምሮት መከባበርን የሚያወግዝ እምነት የለውም፡፡ ሰውን
ማክበር ለራስ ነው የሚባለው ከመንፈሳዊነት አንጻር ብቻ ሳይሆን ራስንም ለማስከበረ ጭምርም ነው፡፡ አንተ ሰው ካላከበርክ ሰው ያከብረኛል ብለኽ የምትጠብቅ ከሆነ ተሳስተሃል! ሰው
የሚያቀል ሰው ላለመቅለሉ ዋስትና ስሌለለው! ስናቀለው የሚያከብረን እየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ የአንድ ሰውን ክብር ነክተህ
ሰውዬው ያከብረኛል ብለህ የምታሰብ ከሆነ ትንሽ ነካ ያደርግሃል ማለት ነው፡፡ ሰውዬው ስታቀለው ምላሽ ካልሰጠህ አንደኛ ንቆህ
ትቶሃል፣ አለበለዚያ ጉልበተኛ መሆንህን ካወቀ ጉልበትህ አስፈርቶታል፣ ወይም ያለበት ሁኔታ አጸፋ ለመስጠት የማያመች እንደሆነ
ተረድቷል፣ ሌላም ሌላም ልንል እንችላለን፡፡ ይህ እንግዲህ በግለሰብ ደረጃ ነው፡፡ በአገርና በተቋም ደረጃ ሲሆን
ማክበርና አለመከበር እንዴት ይሆን መልኩ እኔም እጠይቃለው፡፡
ባለፈ ሳምንት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ለአርቲስት
ተስፋዬ አበበ፣ለአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ እና ለሁለት የውጭ ሀገር ተወላጆች ስጥቷል፡፡ ክብር ለሚገባቸው ክብር መስጠት የአንድ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከመማር ማስተመር ሂደቱ ጎን ለጎን ሌላው ዓላማ ሊሆን የሚገባው ነው፡፡ ለእነዚህ አገራቸውን በቅን
ልቦና ለአገለገሉና ላስጠሩ ግለሰቦች ክብር መስጠት ትክክል ነው እላለው፡፡ ነገር ግን የሀገራችን ከፍተኛ የትምሀርት ተቋማት
የክብር ዶክትሬት ሲሰጡ ምን ይሆን መስፈርታቸው ብለን ብንጠየቅና እስከ ዛሬ የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸውን ግለሰቦች ወይም
አካላቶችንማንነታቸውን በንፈትሽ በተለይ አሁን አሁን አካሄዱ ላይ
መስመር ሊለቅ እንደሚችል መጥርጠር ሟርተኛ ሊያስብል
የሚያስችል አይደለም፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በዚህ ዓመት በማስተርስ ድግሪ የተመረቀ
የመገናኝ ብዙኃን ባለሞያ የሆነ ጋደኛዬ በተመረቀ በማግሰቱ ፒያሳ አካባቢ ሻይ እየጠጣን ስለምረቃ ስናወራ ድንገት ስሜን ጠራና እኔ ምልኽ ይሄ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥን አስተውለኽዋል?!
ዝም ብዬ ሁኔታውን በእርጋት ሳስተውለው አካሄዱ ትንሽ ጤነኛ አልመስልህ አለኝ፡፡ የተለያየ ክልል ያሉ ዩኒቨርስቲዎች የክልላቸው
ተወላጅ ላይ አተኩረው የክብር ዶክትሬት የመስጠት አዝማሚያን ታይባቸዋል በማለት የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸው ግለሰቦችንና የክልሉን ዩኒቨርስቲ እየዘረዘረ አወጋኝ፡፡ እኔም
በሌላ አቅጣጫም ለኔ የሚታየኝ ነገር አለ በማለት የታየኝን ሁኔታ
በማብራራት በጉዳዩ ላይ ለረጅም ሰዓት ተወያየን፡፡
ይህንን ውይይት ለአንባቢ ባዘጋጀው ጥሩ ነው ብዬ ይህን ጹህፍ ላዘጋጅ
ተነሳው፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታችሁና ችግራችሁ እንዲነቀስ የማፈልትፈልጉ ግለሰቦች ወይም አካላት በዚህ ጹህፍ የማነሳው ሀሳብ
ባይጥማችሁም በእርጋታ ወይም በሰከነ መንፈስ ራሳችሁን ልትፈትሹ የግድ ስለሆነ በትግስት ተከታተሉኝ፡፡ (የዚህ ጹህፍ አዘጋጅ
በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ሆነው ችግራችሁ ከማሳየት ይለቅ በዝምታ ከሚተባበራችሁ አለበለዚያ ሙህርነታቸው አስስኪዘነጋቸው ድረስ አመክኖያዊ
ባልሆነ ክርክር፣ አይኔን ግንባር በያድርገው መንፈስ አይነት የአንድ ወገን ወሬ ብቻ በየቴሌቪዥንና በሬድዮ በማውራት ነጥብ
ሊያስመዘግቡ የሚፍጨረጨሩ ግለሰቦች ወይም አካላት በተቃራኒ የእናንተን ችግር እየነቀሰ በማውጣት ለህዝቡ ማሳየት የዜግነት
ግዴታው አድርጎ ነው የሚወስደው፡፡ ለምን አልተወደስንም ለምትሉ አደገኛ የሆነ አካሄዳችሁን እያየሁ የሚያወደስ ህሊና ስለሌለኝ ላወድስ
አልችልምና ተስፋ ቁረጡ በማለት በዚህ አጋጣሚ ሀሳቤን እገልጻለው፡፡ ይህ ደግሞ ህገ መንግስታዊ መብታችን ነው፡፡ ጥቀስ ዋቢ
ከተባልኩ ይህው አንቀጽ-29 አመለካከትንና አስተሳሰብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት)
የዚህ የክበር ዶክትሬት መስጠት የጨዋታ ሜዳ ጉዳይ በሁለት ምድብ ከፍዬ
ባይ ጥሩ ማስረዳት ይቻላል ብዬ አሰብኩ፡፡ አንደኛው ለክብር ዶክትሬት የሚታጩ ሰዎች እንዴት ነው የሜታጩት ወይም መስፈርቱ በማን ዓይን የሚታይ ነው፤ ሁለተኛው የየክልል
ዩኒቭርስቲዎች የክልላቸውን ተወላጅ እየመረጡ ማክበር ከሀገራዊነቱ ይልቅ ክልላዊ ወይም ብሔረሰባዊ አይሆንም ሆይ የሚሉ ሀሳቦች
ናቸው፡፡
ምን
አይነት መስፈርት ይዘን ነው ክብር የምንሰጠው?
መስፈርቱ ምንድን ነው ስንል ለሀገሩ የሚጠቅም ትርጉም ያለው ሥራ የሠራና
ሀገሩን በተለያየ መልክ ያስጠራ በማለት መጠቅለል ይህ ፁህፍ ለተነሳበት ዓላማ ኢለመንተሪ ትረጉም ነው፡፡
የሚያከራክርክም ጉዳይ አይደለም፡፡ መሠረታዊ ችግሩ
ለሀገር ጠቃሚ ወይም ትረጉም ያለው ሥራ ሠራ ወይም ሠራች ሲባል ምን፣ ምን ስትሠራ ወይም ሲሠራ ነው? በማንስ
ዓይን ነው ለሀገሩ ፋይዳ ያለው ስራ ተስርቷል
በሚል የሚመዘነው? አሁንም በሆነ ኮሚቴ ተመልምሎ በዩኒቭርስቲው
አካዳሚክ ኮሚሽን ወይም በሰኔቱ ሲጸድቅ በማለት መልስ መስጠት የወረደ ምላሽ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ሥነስርዓት (procedure)
ሊኖር እነደሚችልም መገመት ከባድ አይደለም፡፡
አሁን እያየን ያለነው የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ በሰኔት ወይም
አካዳሚክ ኮሚሽን የተሰባሰቡ የመንግስት ዕንባ ጠባቂ ሙህራን አይን ከዚህ
ካለፈም በተለያየ ገፊ ምክንያት በመንግስት ባለሠልጣን
የተለመደ የቀጠነች ትዕዛዝ የሚሠጥስ አለመሆኑ ምን ዋስትና
አለው፡፡ መስፈርቱስ መንግስትን አለመቃወም፣ የመንግስት ልማት ሰበብ ስብሰባዎች ላይ መገኘት፣ የመንግስት ፖሊሲን አይን ጨፍኖ በማጨብጨብ እነክን የለሽ ሥራ
በማለት በተለየያ አጋጣሚ መቦትለክ አይደለም ልንልስ ምን ማስረጃ ማቅረብ እንችላለን፡፡ መሬት ላይ ወድቆ የምናየው ነገር ግን የክብር ዶክትሬት እየተባለ የሚሰጣቸው ሰዎች
ክብር የሚገባቸው ያሉ ያኽል ከዚህ ውጪ በሆነ መንገድም እየተሰጠ ላለመሆኑ እንድንጠራጠር አድርጎናል፡፡ ለዚህ ነው መስፈርቱ
ምንድን ነው በማንስ አይን ይመዘናል ብለን የምንጠይቅ? ይሄን ጥያቄ ሳነሳ አንደኛው ምክንያቴ ለሀገራቸው እምብዛም ፋይዳ ያለው ሥራ አልሰሩም ወይም ከእነሱ አስር እጅ የሚያስከነዳ ሥራ የሠሩ ምርጥ የሀገሪቱ ባለውለታ
ኢትዮጵያኖች ዞር ብሎ የሚያያቸው ጠፍቶ የአየንበት ሁኔታ ስለአለ እና የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ወይም መንግስት ጣልቃገብነት
የማይታይበት ተቋም አለ ማለት የማይቻልበት ሁኔታ ስለአለ ጭምርም
ነው፡፡
ስለሀገር ማገልገል፣ስለሀገር ውለታ መስራት መስፈርት አድርገን
የምናወራ ከሆነ አንድ ግለሰብ ወይም ቡድን የክብር ዶክትሬት
ለማግኘት የመንግስት ደጋፊ፣ የመንግሰት ፖሊሲ አራማጅ፣ወይም የኢህአዴግ አቀንቃኝ መሆን አይጠበቅበትም፡፡ ሀገሩን ማገልገል
ለሀገሩ ፋይዳ ያለው ሥራ መሥራት እንጂ! ምክንያቱም ሁለቱም የተለያየ
ጉዳዮች ስለሆኑ፡፡
የፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪዎች አገርና መንግስት የተለያየ እንደሆኑ ትሩጉም በማሰቀመጥ ጭምር ይተነትናሉ፡፡ በእርግጥ አገርንና መንግስትን ነጣጥሎ
ማየት ከባድ ነው ልክ እንደ ሥጋና ደም (blood &
flesh) የመለየት ያክል የሚከብድ ነው የሚሉ ያሉ ቢኖሩም፡፡ አብዛኛው የፖለቲካ ሳይንስ ፈላሰፋዎች የአንድ አገር ዜጋ
አገሩን በጭራሸ መጥላት የለበትም፣ አገሩን የሚጎዳ ተግባር በፍጹም ማድረግ የለበትም፡፡ አገሩን የሚመራ ገዢ መንግሰትን
ግን ሊቃወም፣ ሊጠላ፣ ላይተባበር የመቻል መብት አለው ይላሉ፡፡
ምክንያቱም አገርና መንግስት ይለያያልና! ሀገር (state)ሁሌ የምትኖር ቋሚ ስትሆን መንግሰት(government)ግን በተለያየ
አጋጣሚ ሊቀያየር የሚችል ጊዜያዊ አካል ነው፡፡ መንግስት አንድ የአስተዳደር አይነት፣ የሆነ ሲስተም፤ ለመጥቀስ ያህል
ዲሞክራቲክ፣ ሪፓብሊክ፣ ክሊፖክራቲክ፣ ቴክኖክራሲ፣ኮሚኒስት፣ ወታደራዊ፣ዲክታተርሺፕ፣ፋሺዚዝም፣አርስቶክራሲ፣ኢትኖክራሲ፣ሞናርኪ፣ኦሊጋርኪ፣ጂኖክራሲ፣
ወዘተረፈ በህዝብ ስም ህዝብን ለማሰተዳደር የቆመ ኃይል ሲሆን ሀገር ግን ከዚህ ይለያል፡፡ ሀገር ሌላው ቀርቶ መንግስትንም
በውስጡ ያጠቃልላል፡፡ ሀገር(state) ስንል ቋሚ ሰፋሪ ህዝቦች ያሉት፣ የራሱ የግዛት ክልል ያለው፣መንግስት ያለው፣ከሌሎች
ሀገራት ጋር ግንኙነት የማድረግ አቅም ያለው ነው በማለት ይተነተናል፡፡
ይህንን ሳይንሳዊ ሃቅ ያነሳሁት ለሀገር ማገልገል ለመንግሰት
ካአለማገልገል ጋር መያያዝ የለበትም ለማለት ነው፡፡ በዚህ
የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ላይ መንግሰትን አለመደገፍ ሀገርን ካለማገልገል ጋር መያያዝ የለበትም፡፡ ጥያቂዬም እውን ምንአልባት
ሀገራቸውን በሚገባ ያገለገሉ ህዝብ እንደ አይን ብሌናቸው የሚያያቸው አለም ከወንበሩ ተነስቶ ያጨበጨበላቸው፣ የሀገራችን
ባለውለታዎች ነገር ግን ለመንግስት የማያሸረግዱ ሰዎችና ሥራቸው ከክብር ዶክትሬቱ በበለጠ እየጩኽ የሚናገር የከብር ዶክትሬት
ተደጋግሞ ሊሰጣቸው የሚገባቸው ግና ያሉበት ሁኔታ እንኳን ያልታየ፣ ዳተኛ የአንድ ወገን ለፋፊ መገናኛ ብዙሓንም አይቶ እንዳላየ
እና ትናናሾችን የሌለ ቁመት በመስጠት ከፍ ክፍ ባመድረግ ወይም ህዝቡ በሚገባ ጀግናዎቹን እንዳያውቅ በመከለል፣ አፍኖ የያዛቸው
ግለሰቦች ወይም አካላቶች የሉም?! የሉም የሚል ደፋር ከመጣ
እንሰማለን፡፡
ክልላዊ
ወይም ብሔረሰባዊ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ!
በክብር
ዶክትሬት አሰጣጥ ላይ ሁለተኛው የስጋት አዝማሚያ የሆነው
የየክልል ዩኒቭረስቲዎች የክልላቸው ተወላጅን እየጠሩ የክበር ዶክትሬት ይገባሃል በማለት ክብር የመስጠታቸው ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል አሊ ቢራ ጅማ ዩኒቨርስቲ፣ አስቴር አወቀ ጎንደር
ዩኒቨርስቲ፣የመቀሌ ዩኒቭርስቲ ----- ወዘተ… የክብር
ዶክተሬት ከሰጣቸው ግለሰቦች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የክልል ዩኒቭርስቲዎች ክብር ይገባዋል ብለው ያሉትን ግለሰብ ወይም አካል ማክበራቸው ሰህተት የለውም፡፡ ችግሩ ይህ ከአገር
አልፎ ተርፎም አለማቀፋዊ ፋይዳ ያለው ሥራ የሰራን
ሰው ለማክበር በማሰብ የተዘየደ የክብር ዶክትሬትን የክልላችን ተወላጅን እየጠራን ስንሸልም ከዘርና ከጎሳ ወይም
ከጠባብነት ጋር እንዳይያያዝ ምንያህል ተጠንቅቀናል፡፡ ይህ አይነት
አካሄድስ ሊያስከትል የሚችለውን አጉል አርአያነት አስተውለነው ይሆን? ነገ የወደወላወቡ ዩኒቨርሰቲ የሀገሬውን
ተወላጅን፣ የሰመራ ዩኒቨርሰቲ አፋር የሆነውን ግለሰብ ፣ዋቸሞ ዩኒቭርስቲ የሀገሬውን ተወላጅ ወዘተ እየጠሩ በፉክክር የክብር
ዶክትሬት በየጊዜው ላለማከናነባቸው ምን ዋስትና አለን፡፡
ሲጠቃለል!
የክብር ዶትሬት በሌላው ዓለም ለሀገራቸው
አልፎም ተርፎ ለዓለም ህዝብ ጠቃሚና ፋይዳ ያለው ስራ ለሰሩት ግለሰቦች ወይም አካላት የሚሰጠውን ያህል በአገራችንም
ለአገራቸው ፋይዳ ያለው ሥራ ለሰሩ መስጠቱ ትክክልና ተገቢ ነው፡፡
ለዚህም፡-
·
የክብር ዶክትሬት ሲሰጥ የመንግስት ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ
ያልሆኑትን ግለሰቦች ወይም አካለትን መጠነኛ ሥራቸውን በማጎን በመሸለም ማዕረጉን ከመከበሪያነት ይልቅ የሌላ ሁኔታ መገለጫ
እንዳይሆን በትክክል ለሀገር ያገለገሉትን በፖለቲካዊ ወገንተኝነት (politicize) ሳይቃኝ በንጹሁ ህሊና ለመንግሰት ብቻ ሳይሆን
ለሀገርና ለሀገር ማገልገልን መሠረት ያደረገ ምልመላ ቢደረግ!
·
በየክልል ዩኒቭርሰቲዎች የሚሠጡ የክብር ዶክትሬቶች በወንዝና
በትውልድ ሥፋራ መነሻነት በወገንተኝነት የሚሰጥ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያደረገ፤ማንኛውም የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲ ለሀገራችን ኢትዮጵያ
መሥራትን ማዕከል ያደረገ ክብር መስጠት እንዲከናወን መልክ ማሰያዝ ተገቢ ነው፡፡
·
የመንግስት ረጅም እጅ ለክብር ዶክትሬት እጩ መልማዮች ላይ ጫና
የማይፈጥርበት ሁኔታ መፍጠር፣ምንዓልባትም በአካዳሚክ ኮሚሽን ወይም
ሴኔት ስም ተቀምጠው በእጅ አዙር የሚያሰመለምሉ ወይም የሚያጽድቁ ካድሬዎች ካሉ ወይም ጫና ፈጣሪ ካድሬ ተካቶ ከሆነ፤ የተለመደ
የጣልቃ ገብነት ሚናቸውን በመተው እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ነጻ ትውልድ ቀራጭ ምሁር የፓርቲያቸውን ሥራ ለዚህ ጉዳይ
አንኳን ቢሆን በማቆም እጁን ወይም እጃቸውን ቢሰበስቡ ይመከራል፡፡
·
በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመንግሰት መገናኛ ብዙሐን
የህዝብን ጥቆማና አስተያየት እንፈልጋለን በሚል እንደሚለፈፈው (በእርግጥ ይሄ አሠራር ሙሉ ለሙሉ ወገንተኝነትን ያስቆማል
ባይባልም፤) ለዶክትሬት ክብር ህዝቡ ይገባዋል ወይም ይገባቸዋል የሚላቸውን የእርሱ ባለውለታዎችን እንዲጠቁምና አስተያየት
እንዲሰጥ ሁኔታዎች የተመቻቸ ቢሆን፡፡
·
የክብር ዶክትሬቱ ሀገርቀፋዊነቱን መሰረት አድርጎ አለማቀፋዊ
ፋይዳም ታሳቢ ቢደረግበት አሁን እያየን ያለነውን አደገኛ
አዝማሚያ መልክ ያስይዛል፡፡
ክብሩ በእውነት ለሀገር ያገለገሉትን ሳይሆን ከላይ በገለጽነው መልኩ
በወገንተኝነት እና የተወሰነ ህብረተሰብን ክፍል በማግለል የሚታደል አይነት ከሆነ በቅርብ ዓመታቶች በህዝቡ ዘንድ የክብር
ዶክትሬቱ ተቀጽላ ሥም አይሰጠውም ወይም የሌላ አሉታዊ መገለጫ አይሆንም ማለት አይቻልም፡፡ በዝራው አሻግሬ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ