ዓርብ 25 ጁላይ 2014

የክብር ዶክትሬትና የጨዋታ ሜዳው!



የክብር ዶክትሬትና የጨዋታ ሜዳው!
     
       መከበር የሚገባውን ሰው ማክበር ለተከበረው ግለሰሰብ ብቻ ሳይሆን ራስንም ጭምር ያስከብራል፡፡ በግለሰብ ደረጃ የሰው ልጆችን ሀብት፣ሃይማኖት፣አስተሳሰብ፣ዕድሜ፣ዘር ሳይለዩ ማክበር ተገቢ ከመሆኑ ባሻገር የህሊና እርካታም ይሰጣል፡፡ የማንኛውም ሃይማኖት አስትምሮት  መከባበርን የሚያወግዝ እምነት የለውም፡፡ ሰውን ማክበር ለራስ ነው የሚባለው ከመንፈሳዊነት አንጻር ብቻ ሳይሆን ራስንም ለማስከበረ ጭምርም ነው፡፡ አንተ ሰው  ካላከበርክ ሰው ያከብረኛል ብለኽ የምትጠብቅ ከሆነ ተሳስተሃል! ሰው የሚያቀል ሰው ላለመቅለሉ ዋስትና ስሌለለው! ስናቀለው የሚያከብረን እየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ የአንድ ሰውን ክብር ነክተህ ሰውዬው ያከብረኛል ብለህ የምታሰብ ከሆነ ትንሽ ነካ ያደርግሃል ማለት ነው፡፡ ሰውዬው ስታቀለው ምላሽ ካልሰጠህ አንደኛ ንቆህ ትቶሃል፣ አለበለዚያ ጉልበተኛ መሆንህን ካወቀ ጉልበትህ አስፈርቶታል፣ ወይም ያለበት ሁኔታ አጸፋ ለመስጠት የማያመች እንደሆነ ተረድቷል፣ ሌላም ሌላም ልንል እንችላለን፡፡ ይህ እንግዲህ በግለሰብ ደረጃ ነው፡፡ በአገርና በተቋም ደረጃ ሲሆን ማክበርና  አለመከበር እንዴት ይሆን መልኩ እኔም እጠይቃለው፡፡
   ባለፈ ሳምንት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ለአርቲስት ተስፋዬ አበበ፣ለአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ እና ለሁለት የውጭ ሀገር ተወላጆች ስጥቷል፡፡ ክብር ለሚገባቸው ክብር መስጠት የአንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከመማር ማስተመር ሂደቱ ጎን ለጎን ሌላው ዓላማ ሊሆን የሚገባው ነው፡፡ ለእነዚህ አገራቸውን በቅን ልቦና ለአገለገሉና ላስጠሩ ግለሰቦች ክብር መስጠት ትክክል ነው እላለው፡፡ ነገር ግን የሀገራችን ከፍተኛ የትምሀርት ተቋማት የክብር ዶክትሬት ሲሰጡ ምን ይሆን መስፈርታቸው ብለን ብንጠየቅና እስከ ዛሬ የክብር ዶክትሬት የተሰጣቸውን ግለሰቦች ወይም አካላቶችንማንነታቸውን በንፈትሽ በተለይ አሁን አሁን አካሄዱ ላይ   መስመር ሊለቅ  እንደሚችል መጥርጠር ሟርተኛ ሊያስብል የሚያስችል አይደለም፡፡ 
  በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በዚህ ዓመት በማስተርስ ድግሪ የተመረቀ የመገናኝ ብዙኃን ባለሞያ የሆነ ጋደኛዬ በተመረቀ በማግሰቱ ፒያሳ አካባቢ ሻይ እየጠጣን ስለምረቃ ስናወራ ድንገት  ስሜን ጠራና እኔ ምልኽ ይሄ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥን አስተውለኽዋል?! ዝም ብዬ ሁኔታውን በእርጋት ሳስተውለው አካሄዱ ትንሽ ጤነኛ አልመስልህ አለኝ፡፡ የተለያየ ክልል ያሉ ዩኒቨርስቲዎች የክልላቸው ተወላጅ ላይ አተኩረው የክብር ዶክትሬት የመስጠት አዝማሚያን ታይባቸዋል በማለት የክብር ዶክትሬት  የተሰጣቸው ግለሰቦችንና የክልሉን ዩኒቨርስቲ እየዘረዘረ አወጋኝ፡፡ እኔም በሌላ አቅጣጫም ለኔ የሚታየኝ ነገር አለ በማለት የታየኝን ሁኔታ  በማብራራት በጉዳዩ ላይ ለረጅም ሰዓት ተወያየን፡፡
    ይህንን ውይይት ለአንባቢ ባዘጋጀው ጥሩ ነው ብዬ ይህን ጹህፍ ላዘጋጅ ተነሳው፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታችሁና ችግራችሁ እንዲነቀስ የማፈልትፈልጉ ግለሰቦች ወይም አካላት በዚህ ጹህፍ የማነሳው ሀሳብ ባይጥማችሁም በእርጋታ ወይም በሰከነ መንፈስ ራሳችሁን ልትፈትሹ የግድ ስለሆነ በትግስት ተከታተሉኝ፡፡ (የዚህ ጹህፍ አዘጋጅ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ሆነው ችግራችሁ ከማሳየት ይለቅ በዝምታ ከሚተባበራችሁ አለበለዚያ ሙህርነታቸው አስስኪዘነጋቸው ድረስ አመክኖያዊ ባልሆነ ክርክር፣ አይኔን ግንባር በያድርገው መንፈስ አይነት የአንድ ወገን ወሬ ብቻ በየቴሌቪዥንና በሬድዮ በማውራት ነጥብ ሊያስመዘግቡ የሚፍጨረጨሩ ግለሰቦች ወይም አካላት በተቃራኒ የእናንተን ችግር እየነቀሰ በማውጣት ለህዝቡ ማሳየት የዜግነት ግዴታው አድርጎ ነው የሚወስደው፡፡ ለምን አልተወደስንም ለምትሉ አደገኛ የሆነ አካሄዳችሁን እያየሁ የሚያወደስ ህሊና ስለሌለኝ ላወድስ አልችልምና ተስፋ ቁረጡ በማለት በዚህ አጋጣሚ ሀሳቤን እገልጻለው፡፡ ይህ ደግሞ ህገ መንግስታዊ መብታችን ነው፡፡ ጥቀስ ዋቢ ከተባልኩ ይህው አንቀጽ-29 አመለካከትንና  አስተሳሰብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ መብት) 
  የዚህ የክበር ዶክትሬት መስጠት የጨዋታ ሜዳ ጉዳይ በሁለት ምድብ ከፍዬ ባይ ጥሩ ማስረዳት ይቻላል ብዬ አሰብኩ፡፡ አንደኛው ለክብር ዶክትሬት የሚታጩ ሰዎች እንዴት ነው  የሜታጩት ወይም መስፈርቱ በማን ዓይን የሚታይ ነው፤ ሁለተኛው የየክልል ዩኒቭርስቲዎች የክልላቸውን ተወላጅ እየመረጡ ማክበር ከሀገራዊነቱ ይልቅ ክልላዊ ወይም ብሔረሰባዊ አይሆንም ሆይ የሚሉ ሀሳቦች ናቸው፡፡    
     ምን አይነት መስፈርት ይዘን ነው ክብር የምንሰጠው?
  መስፈርቱ ምንድን ነው ስንል ለሀገሩ የሚጠቅም ትርጉም ያለው ሥራ የሠራና ሀገሩን በተለያየ መልክ ያስጠራ በማለት መጠቅለል ይህ ፁህፍ ለተነሳበት ዓላማ ኢለመንተሪ ትረጉም  ነው፡፡  የሚያከራክርክም ጉዳይ አይደለም፡፡ መሠረታዊ ችግሩ  ለሀገር ጠቃሚ ወይም ትረጉም ያለው ሥራ ሠራ ወይም ሠራች ሲባል ምን፣ ምን ስትሠራ ወይም ሲሠራ ነው?  በማንስ  ዓይን ነው ለሀገሩ ፋይዳ ያለው  ስራ ተስርቷል በሚል  የሚመዘነው? አሁንም በሆነ ኮሚቴ ተመልምሎ በዩኒቭርስቲው አካዳሚክ ኮሚሽን ወይም በሰኔቱ ሲጸድቅ በማለት መልስ መስጠት የወረደ ምላሽ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ሥነስርዓት (procedure) ሊኖር እነደሚችልም መገመት ከባድ አይደለም፡፡  
    አሁን እያየን ያለነው የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ በሰኔት ወይም አካዳሚክ ኮሚሽን የተሰባሰቡ የመንግስት ዕንባ ጠባቂ ሙህራን አይን ከዚህ  ካለፈም በተለያየ ገፊ ምክንያት  በመንግስት ባለሠልጣን የተለመደ የቀጠነች ትዕዛዝ የሚሠጥስ አለመሆኑ ምን ዋስትና  አለው፡፡ መስፈርቱስ መንግስትን አለመቃወም፣ የመንግስት ልማት ሰበብ ስብሰባዎች ላይ  መገኘት፣ የመንግስት ፖሊሲን አይን ጨፍኖ በማጨብጨብ እነክን የለሽ ሥራ በማለት በተለየያ አጋጣሚ መቦትለክ አይደለም ልንልስ ምን ማስረጃ ማቅረብ እንችላለን፡፡ መሬት ላይ  ወድቆ የምናየው ነገር ግን የክብር ዶክትሬት እየተባለ የሚሰጣቸው ሰዎች ክብር የሚገባቸው ያሉ ያኽል ከዚህ ውጪ በሆነ መንገድም እየተሰጠ ላለመሆኑ እንድንጠራጠር አድርጎናል፡፡ ለዚህ ነው መስፈርቱ ምንድን ነው በማንስ አይን ይመዘናል ብለን የምንጠይቅ? ይሄን ጥያቄ ሳነሳ አንደኛው  ምክንያቴ ለሀገራቸው እምብዛም ፋይዳ ያለው ሥራ አልሰሩም ወይም  ከእነሱ አስር እጅ የሚያስከነዳ ሥራ የሠሩ ምርጥ የሀገሪቱ ባለውለታ ኢትዮጵያኖች ዞር ብሎ የሚያያቸው ጠፍቶ የአየንበት ሁኔታ ስለአለ እና የገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ወይም መንግስት ጣልቃገብነት የማይታይበት ተቋም አለ ማለት የማይቻልበት ሁኔታ ስለአለ ጭምርም  ነው፡፡  
    ስለሀገር ማገልገል፣ስለሀገር ውለታ መስራት መስፈርት አድርገን የምናወራ ከሆነ አንድ  ግለሰብ ወይም ቡድን የክብር ዶክትሬት ለማግኘት የመንግስት ደጋፊ፣ የመንግሰት ፖሊሲ አራማጅ፣ወይም የኢህአዴግ አቀንቃኝ መሆን አይጠበቅበትም፡፡ ሀገሩን ማገልገል ለሀገሩ ፋይዳ  ያለው ሥራ መሥራት እንጂ! ምክንያቱም ሁለቱም የተለያየ ጉዳዮች ስለሆኑ፡፡ 
  የፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪዎች አገርና መንግስት የተለያየ እንደሆኑ ትሩጉም  በማሰቀመጥ ጭምር ይተነትናሉ፡፡ በእርግጥ አገርንና መንግስትን ነጣጥሎ ማየት ከባድ ነው  ልክ እንደ ሥጋና ደም (blood & flesh) የመለየት ያክል የሚከብድ ነው የሚሉ ያሉ ቢኖሩም፡፡ አብዛኛው የፖለቲካ ሳይንስ ፈላሰፋዎች የአንድ አገር ዜጋ አገሩን በጭራሸ መጥላት የለበትም፣ አገሩን የሚጎዳ ተግባር በፍጹም ማድረግ የለበትም፡፡ አገሩን የሚመራ ገዢ መንግሰትን ግን  ሊቃወም፣ ሊጠላ፣ ላይተባበር የመቻል መብት አለው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም አገርና መንግስት ይለያያልና! ሀገር (state)ሁሌ የምትኖር ቋሚ ስትሆን መንግሰት(government)ግን በተለያየ አጋጣሚ ሊቀያየር የሚችል ጊዜያዊ አካል ነው፡፡ መንግስት አንድ የአስተዳደር አይነት፣ የሆነ ሲስተም፤ ለመጥቀስ ያህል ዲሞክራቲክ፣ ሪፓብሊክ፣ ክሊፖክራቲክ፣ ቴክኖክራሲ፣ኮሚኒስት፣ ወታደራዊ፣ዲክታተርሺፕ፣ፋሺዚዝም፣አርስቶክራሲ፣ኢትኖክራሲ፣ሞናርኪ፣ኦሊጋርኪ፣ጂኖክራሲ፣ ወዘተረፈ በህዝብ ስም ህዝብን ለማሰተዳደር የቆመ ኃይል ሲሆን ሀገር ግን ከዚህ ይለያል፡፡ ሀገር ሌላው ቀርቶ መንግስትንም በውስጡ ያጠቃልላል፡፡ ሀገር(state) ስንል ቋሚ ሰፋሪ ህዝቦች ያሉት፣ የራሱ የግዛት ክልል ያለው፣መንግስት ያለው፣ከሌሎች ሀገራት ጋር ግንኙነት የማድረግ አቅም ያለው ነው በማለት ይተነተናል፡፡
   ይህንን ሳይንሳዊ ሃቅ ያነሳሁት ለሀገር ማገልገል ለመንግሰት ካአለማገልገል ጋር መያያዝ  የለበትም ለማለት ነው፡፡ በዚህ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ላይ መንግሰትን አለመደገፍ ሀገርን ካለማገልገል ጋር መያያዝ የለበትም፡፡ ጥያቂዬም እውን ምንአልባት ሀገራቸውን በሚገባ ያገለገሉ ህዝብ እንደ አይን ብሌናቸው የሚያያቸው አለም ከወንበሩ ተነስቶ ያጨበጨበላቸው፣ የሀገራችን ባለውለታዎች ነገር ግን ለመንግስት የማያሸረግዱ ሰዎችና ሥራቸው ከክብር ዶክትሬቱ በበለጠ እየጩኽ የሚናገር የከብር ዶክትሬት ተደጋግሞ ሊሰጣቸው የሚገባቸው ግና ያሉበት ሁኔታ እንኳን ያልታየ፣ ዳተኛ የአንድ ወገን ለፋፊ መገናኛ ብዙሓንም አይቶ እንዳላየ እና ትናናሾችን የሌለ ቁመት በመስጠት ከፍ ክፍ ባመድረግ ወይም ህዝቡ በሚገባ ጀግናዎቹን እንዳያውቅ በመከለል፣ አፍኖ የያዛቸው ግለሰቦች ወይም አካላቶች የሉም?! የሉም የሚል ደፋር  ከመጣ እንሰማለን፡፡
 ክልላዊ ወይም ብሔረሰባዊ የክብር ዶክትሬት አሰጣጥ!
 በክብር ዶክትሬት አሰጣጥ ላይ ሁለተኛው የስጋት አዝማሚያ የሆነው የየክልል ዩኒቭረስቲዎች የክልላቸው ተወላጅን እየጠሩ የክበር ዶክትሬት ይገባሃል በማለት ክብር የመስጠታቸው  ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል አሊ ቢራ ጅማ ዩኒቨርስቲ፣ አስቴር አወቀ ጎንደር ዩኒቨርስቲ፣የመቀሌ ዩኒቭርስቲ    ----- ወዘተ… የክብር ዶክተሬት ከሰጣቸው ግለሰቦች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
    የክልል ዩኒቭርስቲዎች ክብር ይገባዋል ብለው ያሉትን  ግለሰብ ወይም አካል ማክበራቸው ሰህተት የለውም፡፡ ችግሩ ይህ ከአገር አልፎ ተርፎም አለማቀፋዊ ፋይዳ  ያለው  ሥራ የሰራን  ሰው ለማክበር በማሰብ የተዘየደ የክብር ዶክትሬትን የክልላችን ተወላጅን እየጠራን ስንሸልም ከዘርና ከጎሳ ወይም ከጠባብነት ጋር እንዳይያያዝ ምንያህል ተጠንቅቀናል፡፡ ይህ አይነት  አካሄድስ ሊያስከትል የሚችለውን አጉል አርአያነት አስተውለነው ይሆን? ነገ የወደወላወቡ ዩኒቨርሰቲ የሀገሬውን ተወላጅን፣ የሰመራ ዩኒቨርሰቲ አፋር የሆነውን ግለሰብ ፣ዋቸሞ ዩኒቭርስቲ የሀገሬውን ተወላጅ ወዘተ እየጠሩ በፉክክር የክብር ዶክትሬት በየጊዜው ላለማከናነባቸው ምን ዋስትና አለን፡፡
      ሲጠቃለል!
የክብር ዶትሬት በሌላው  ዓለም ለሀገራቸው  አልፎም  ተርፎ ለዓለም ህዝብ ጠቃሚና ፋይዳ  ያለው ስራ ለሰሩት ግለሰቦች ወይም አካላት የሚሰጠውን ያህል በአገራችንም ለአገራቸው ፋይዳ  ያለው ሥራ ለሰሩ መስጠቱ ትክክልና ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም፡-
·         የክብር ዶክትሬት ሲሰጥ የመንግስት ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ ያልሆኑትን ግለሰቦች ወይም አካለትን መጠነኛ ሥራቸውን በማጎን በመሸለም ማዕረጉን ከመከበሪያነት ይልቅ የሌላ ሁኔታ መገለጫ እንዳይሆን በትክክል ለሀገር ያገለገሉትን በፖለቲካዊ ወገንተኝነት (politicize) ሳይቃኝ በንጹሁ ህሊና ለመንግሰት ብቻ ሳይሆን ለሀገርና ለሀገር ማገልገልን መሠረት ያደረገ ምልመላ ቢደረግ!
·         በየክልል ዩኒቭርሰቲዎች የሚሠጡ የክብር ዶክትሬቶች በወንዝና በትውልድ ሥፋራ መነሻነት በወገንተኝነት የሚሰጥ እንዳይሆን ጥንቃቄ ያደረገ፤ማንኛውም የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲ ለሀገራችን ኢትዮጵያ መሥራትን ማዕከል ያደረገ ክብር መስጠት እንዲከናወን መልክ ማሰያዝ ተገቢ ነው፡፡
·         የመንግስት ረጅም እጅ ለክብር ዶክትሬት እጩ መልማዮች ላይ ጫና የማይፈጥርበት  ሁኔታ መፍጠር፣ምንዓልባትም በአካዳሚክ ኮሚሽን ወይም ሴኔት ስም ተቀምጠው በእጅ አዙር የሚያሰመለምሉ ወይም የሚያጽድቁ ካድሬዎች ካሉ ወይም ጫና ፈጣሪ ካድሬ ተካቶ ከሆነ፤ የተለመደ የጣልቃ ገብነት ሚናቸውን በመተው እንደ አንድ ኃላፊነት እንደሚሰማው ነጻ ትውልድ ቀራጭ ምሁር የፓርቲያቸውን ሥራ ለዚህ ጉዳይ አንኳን ቢሆን በማቆም እጁን ወይም እጃቸውን ቢሰበስቡ ይመከራል፡፡
·         በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመንግሰት መገናኛ ብዙሐን የህዝብን ጥቆማና አስተያየት እንፈልጋለን በሚል እንደሚለፈፈው (በእርግጥ ይሄ አሠራር ሙሉ ለሙሉ ወገንተኝነትን ያስቆማል ባይባልም፤) ለዶክትሬት ክብር ህዝቡ ይገባዋል ወይም ይገባቸዋል የሚላቸውን የእርሱ ባለውለታዎችን እንዲጠቁምና አስተያየት እንዲሰጥ ሁኔታዎች የተመቻቸ ቢሆን፡፡
·         የክብር ዶክትሬቱ ሀገርቀፋዊነቱን መሰረት አድርጎ አለማቀፋዊ ፋይዳም ታሳቢ ቢደረግበት  አሁን እያየን ያለነውን አደገኛ አዝማሚያ መልክ ያስይዛል፡፡
   ክብሩ በእውነት ለሀገር ያገለገሉትን ሳይሆን ከላይ በገለጽነው መልኩ በወገንተኝነት እና የተወሰነ ህብረተሰብን ክፍል በማግለል የሚታደል አይነት ከሆነ በቅርብ ዓመታቶች በህዝቡ ዘንድ የክብር ዶክትሬቱ ተቀጽላ ሥም አይሰጠውም ወይም የሌላ አሉታዊ መገለጫ አይሆንም ማለት አይቻልም፡፡ በዝራው አሻግሬ

ሐሙስ 10 ጁላይ 2014

ከቴዲ አፍሮ ዘመቻ በስተጀርባ!


ከቴዲ አፍሮ  ዘመቻ በስተጀርባ! 
    አንድ ጊዜ አንድ እራሱን እየተቆጣ ተመርጫለው የሚል ሬድዮ ጣቢያ ላይ የይቅርታና  የእርቅ ፕሮግራም አዘጋጅ ሆኜ  ወቅቱ ፕሮግራሙ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ ሊቀርብ የነበረበት ቀን ነበርና የፕሮግራሙን ፓኬጅ(ተቀርፆ የተዘጋጀ የሬድየ ፕሮግራም)እንዲተላለፍ ለቴክኒሻን
ሰጠው፡፡ ከተወሰነ ሠዓታት በኃለ ፕሮግራሙ አየር ላይ ሲውል ለመከታታል ሬድዮ ጣቢያው  ስመጣ ቴክንሻና የፕሮግራም መግቢያ የሆነው ዘፈን በኃላፊ መቀየር አለበት ተብላል አለችኝ፡፡  ምንድን  ነው  ነገሩ  ዘፈኑ  እኮ  ለፕሮግራሙ  መክፈቻ ተስማሚ  ነው፣ በዚህ  ፕሮግራም  ላይ ደግሞ መግባባትን፣ይቅርታንና እርቅን የሚሰብኩ ዜማዎች እንደምናቀርብ ነው  በፕሮጀክታችን ላይ ያቀረብነው ይሄ ዘፈን  ደግሞ ተገዳደሉ የሚል አይደለም ታረቁ እንጂ  እንጂ አልኩ፤ ወቅቱ  የአዲስ ዘመን አይደለም አይተላለፍም ተባልኩ፡፡ እረ ስለ አዲስ  ዘመን  ብቻ አይደለም የሚያወራው  መሰረታዊ  መልዕክቱ  ጊዜው   የእርቅ  ነው የሚለው አልኩ፤ (ልክ እነድ የተሃድሶ  ዘመን እነደሚባለው  እንዲወሰድልኝ ቃላቶቹን  እየቀለጽኩ)  የሚሰማኝ  ጠፋ፡፡ ወዲያው  በዚህ ሬድዮ  ጣቢያ  መሥራት ፈታኝ  እንደሚሆን  ተገነዘብኩ  በርግጥም  እኔና ባልደረቦቼ ብዙ ፈተነን፡፡ እንደዚህ አይነት ውጣ ውረድ በመንግሰትም ይሁን የመንግስት ደጋፊ የሆኑ መገናኛ ጣቢያዎች ላይ  ከጀርባ  የሚሰሩ የተለመዱ ህግ የሌላቸው እስር ቤቶች መሆኑአቸውን ሬድዮ  ፕሮግራም የማዘጋጀት ልምድ ያላቸው ባለሞያዎች  የለመዱት ችግር  ነው፡፡ ለግንዛቤ እንዲረዳን አይተላለፍም   የተባለው   ዘፈንን  የግጥም  መልዕክት  አስቲ  እንየው፡፡   
ምልኤላዊው ዘመን የአምላክ በረከቱ፣
በኢትዮጵያትንሳኤ ዘመነ..ው ዕለቱ
ስትሰሙ መለከት ወደ ምስራቅ ተመልከቱ!
እነዚህ  ስንኞች የግድ ተሃድሶ የሚል ቃል ይጨመርበት ካልተባለ በስተቀር ወይም  እነሱ  ካላሉት በስተቀር ሌላ ትረጉም የሚሰጥ ካልሆነ በስተቀር ስለ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ነው  የሚያወራው፡፡ አሁንም ዚህው ዜማ ሌላ ስንኝ  ልጨምር፤
ወዲህ ወዲህ ና ተው  ያገሬ ሰው ፣
ሰው ሀገር ሆንህ ሆድክን አይባስው፤
ስንኮራረፍ ጠላት ይስቃል፣
የአገር ሰማይ በማን ይደምቃል፤
ስማህ  ስጠራ በዚህ ማስንቆ፣
ይታወቅ እንጂ ሁሉም ሰው ታርቆ፡፡
     ይህ እንግዲህ ገልብጠን ካላየነው በስተቀር በስደት ያላችሁ ወገኖቼ ሰው አገር ሆናችሁ  ሆድ አይባሳችሁ ወደ አገራችሁ ግቡ፣ስንኮራረፍ ጠላት ይስ ይለዋል፣ ስጠራህ በማሰንቆ ስማ  ሁሉም ሰው ታርቆ ይታይ ነው የሚለው፡፡(በእርግጥ ይህ ሬድዮ ወይም ቴሌቪዥን ቢሆን ጋዜጣ ሆነ እንጂ እንዴት የዜማውን ወደር የሌለው መሆኑንን በድምጽ ከቅንብሩ ጋር  በማስማት ምስክርነታችንን  እንሰጥ  ነበር)
ታዲያ እንግዲ ይህ ዜማ ነው አዲስ ዘመን አይደለም አይቀርብም የተባለው፡፡ ጉዳዩ የአዲስ   ዘመን ጉዳይ እንዳልሆነ ስሌት ሳያስፈልገኝ ተረድቸዋለው ቢሆንም ለሬድዮ ጣቢያ ኃላፊም ለእኔም የሚመጥን ምላሽ አይደለም አሁንም ጥቂት ስንኞች ልሰንዝር፡፡
አርንጋዴና  ቢጫ ቀይ  አርማው፣
ከፍ ይላል  ገና ወጥቶ  ከማማው፤
ሰለሞን አለ ጊዜ  ለኩሉ፣
ይሰግድልሻል የናቀሽ  ሁሉ፤
አሳልፈናል ክፉ ደጉን፣
                               ቃል ኪዳን  አለው  እንዳይለየን፤
ባንድራችን ከማማ ላይ ወጥቶ ከፍ ይላላ የናቁሸ ሁሉ ይሰግዱልሻል ማለት ያስከፋ ይሆን!  አገር ለናቀ ሰው ካልሆነ በስተቀር፡፡ ስንኞቹ በእርግጥ ስለአገር ከወሬ  የዘለለለ ስሜት ለሌለው  ወይም በአገር ስም ለሚነግድ ሰው እውነተኛ አገር ወዳድ በስሜት ተውጦ ስለአገር ሲያወራ  እረፍት ሊነሳ ይችላል፡፡
    የቴዲ አፍሮ ዘፈንኖች እንደዚህ የሰውን ስሜት መግዛት የሚችሉ ዘፈኖች ናቸው፡፡  ከግጥም፣ከዜማ ከቅንብርና ካዘሉት ጠንካራ መልዕክት አንጻር ስናይ ይህ ዜመኛ   የሚስተካከለው የለውም ማለት መሬት የወደቀ እውነት ነው፡፡ ቴዴ አፍሮን በአካል  አላውቀውም፣ የእርሱን የሙዚቃ  ዝግጅቶችንም  አይቼ  አላውቅም፣  ተሳትፌም  አላውቅም  በምንም አጋጣሚ ተገናኝቼው አላውቅም፣ ግን ሙዚቃውን ሳዳምጥ ስሜቴ እንደሚሰጠኝ መናገር እወዳለው፡፡ ወይም ይሄ ስሜት ሰዋሪነቱ የአደባባይ ሚስጥርነቱን ከብዙዎች  ተረድቻለው፡፡ ለዚህ ነው ከፍተኛ ተወዳጅነት በህዝቡ መከካል ያገኘው፣ ለዚህ ነው ሰው   እሱን አትንኩነብኝ የሚለው፡፡ ይህ ሰው የሚማርክ ድምጽ ስላለው፣ ስነ ግጥሞቹ ጠንካር  ስለሆኑ፣ ዜማው በራሱ ስለሚናገር፣ የሙዚቃ ሥራዎቹ በአብዛኛው የእርሱ የአህምሮ ጭማቂ  ውጤት መሆኑ፣ የተመረጡ አቀናባሪዎች ስለአሉት፣ ብቻ አይደለም የሚወደደው፡፡   የአልበሞቹ ጭብጦች ፍቅር  ናቸው፣ ሀገር  ናቸው፣ሰላም  ናቸው፣ ነጻነት ናቸው፣በጥናት የሚሰሩ ናቸው፣ ህሊናዊ መሆንን የሚሰብኩ ናቸው ለሆዳሞች  ህሊና  ለሌላቸው ጣር  ነው  የሚፈጥሩት፡፡ ታገሱኝና  አሁንም  ከሌላ  ዜማው  ደግሞ ተጨማሪ  ስንኝ  ላስነብባችሁ፡፡  ሰላም ይሰኛል ስንኙ፡፡
ዋሽቶ ለመኖር አፌ አይችልም ከቶ፣
ታምኖ ይኖራል እንጂ ያለውን በልቶ፤
ደልቶኝ የሞላ ኑሮ መኖር ባልጠላም፣
ገንዘብ ለማግኝት ብዬ አላጣም ሰላም፣
እኔ አላጣም ሰላም፣
አላጣም ሰላም እኔ አላጣም ሰላም፡፡
    በቀላሉ ዋሽቶ መኖር ጠቃሚ እንዳልሆነ ሰላም እንደሚነሳ የሚሰይ  ዜማ ነው
                    ታዲያ ለምን ዘመቻ?
                 አቅምና ተስጥኦ
     ከላይ  ለማሳየት  እንደመኮርኩት  የቴዎድሮስ  ዜማዎች   በአብዛኛው  የአገር  ፍቅርን የሚሰብኩ መልካምነተን የሚያወድሱ፣ ለሆድ መገዛት የእንሰሳት ባህሪ መሆኑን የሚያመላክቱ፣ በድህነት በህሊና መኖር የሰላም  ባለቤት እንደሚያደርግ፣  ፍቅር  እንደሚያሸንፍ ፣ተስፋ  ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ አድማጩን የሚያበረቱ፣ የህብረተሰቡን  እውነተኛ  ስሜት ፈልቅቆ  በማውጣት  ለህብረተሰቡ  በተለገሰው  ተስጦ  ስሜት  በሚገዛ  መልክ  የሚቀርቡ፣ ለውጥ  የማያመጡ መሪዎችን  በድፍረት የሚገስጹ፣  ስንኞቹ ጨቋኞችን  በእሳት  አለንጋ የሚገርፉ፣ ግፈኞችንና  አሽከሮቻቸውን  ተግባራቸውን በመጠቆም  በቆሙመት የሚያርዱ፣ ታሪክን የሚያውጁ፣  አለምግባባትን  የሚያስታርቁ፣ወዘተ  ናቸው፡፡  ከጥቁር  ሰው አልበም ዜማ አንድ ሁለት ስንኝ ማሳየት  አባባሌን ያጠነክርልኛል ብዬ ስለማስብ የተወሰነ ላክል፡፡
    ጊዮረጊስ  ፈረሱ ቆሞ ሳይ፣
    ድል ቀናኝ ሳልል ዋይ(2)
   አባቴ  ወኔውን   ተኮሰው፣
     ምንሊክ ጥቁር  ሰው፤
    ዳኛው ያሉት አባ መላ  ፊት/ ሐብቴ ዲነግዴ፣
ስልፉን በጦር አስምረው  ፊት ሆኖ በዘዴ፤
ሳልል ዋይ፣
ሳልል  ዋይ፡፡
ምኒሊክ ጥቁር ሰው ወኔን ይጭራል ዋይ! ዋይ! ሳልል በዘዴ ድል ቀናን በማለት የምኒልክን ጥበብ ጀግንነት በማሰየት በሚኒልክ ላይ የሚነሳውን  ከኦሮሞ ጋር የተያያዘ አሉታዊ ጉዳይ  በጥበብ  ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ለማግባባት ዜማውን በኦሮምኛ ስልት መሀል መሀል  ላይ የኦሮምኛ ግጥም በማስገባት ሰላም ለማውረድ ሲጥር ይታያል፡፡
ወይ ሳልላት ብቅር ያኔ፣
እኔን አልሆንም ነበር ያኔ፤
ኢጆሌ ቢያኮ ጀጀባዳ መሌ፣
ጀዴቶ ከኤ ያገሬ  ኮበሌ፤
      ዱበት ኢንደዴምኑ እልከንተኤ  ጉያ፣
ዲናፍ ኢላኑ ኢትዮጵያ፡፡
ጀዴ!
                     ስብዕና 
   ቴዎድሮስ  በግል ባህሪው ፍጹም ነው እንከን የለበትም ብለን ለመናገር የሚከብድ ቢሆንም በተለይ  በአገር  ጉዳይ ጠንካራ ስብዕና እና  አስተዋይ አህምሮ እንዳለለው  መናገር  ይቻላል ፡፡  ይህ  ሰው ህዝቡን አክባሪ፣ ለፕሮፓጋንዳ  ፍጆታ ሞያውን  የማያውል፣ ገንዝበ የማይደልለው፣ እያንዳንዱ እንቅስቃሴውን እንደ  መልካም  መሪ  ከሚወደው  ህዝብ ፍላጎትና  ጥቅም  ጋር  የሚያይይዝ፣ (በአሁኑ  ዘመን  ቀላል  የማይባለ  የፖለቲካ  መሪዎች፣ ታዋቂ  ሰዎች ፣ሙህራኖች  ባለሀባቶች፣ የህዝብ ናቸው የሚባሉ  የኪነጥበብ  ሰዎች ጓዛቸውን  ጠቅልለው  ወደ  ምንም አላየንም ቡድን  ሲጠቃለሉና ሀሰት  ሲሰብኩ  በነፈሰበት የማይነፍስ  ጸንቶ የቆመ የኪነጥበብ ሰው  ነው፡፡ ) በተገኘው  አጋጣሚ  መልካም ሥራ  በመስራት ቀናኢነቱናና  አርአያነቱን የሚያሳይ  ነው፡፡
                 የህዝብ  ፍቅር 
የዕድሜ ፣ፆታ ፣የሃይማኖት፣ የማህበራዊ ማንነት፣ የሞያ  አይነት፣የእውቀት  ደረጃ  ሳይወስነው ከፍተኛ የሆነ የህዝብ  አድናቆትና ድጋፍ ያለው  ነው፡፡ በእሱ ዝግጅቶች፣ በእርሱ ሙዚቃዎች ሰዎች በስሜት ይናጣሉ፣ እራሳቸውን  ወደ ውስጥ ያያሉ፣ ስለፍቅር  ስለሃገር ያስባሉ፣ በሰሜት ይተቃቀፋሉ፣ ኢትዮጵያዊነት ውስጣቸው  ይሰርፃል፡፡ ህዝቡ  የእሱን ፍቅርና  ለመግለጽና  በዜማው የሚያስተላልፈውን መልዕክት ለመቋደስ የሙዚቃ  አልበሙን  በውድ  ዋጋ  ሆዱን  እየራበው ስልፎ ይዞ  በመግዛት አክብሮቱን ያሳያል፡፡
           በስተጀርባ
   ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ሚስጥሩ የጠፋቸው ባይሆንም ቴዎድሮሰ ካሰሁን  ምንድን ነው ጥፋቱ? ብለው በቴዎድሮስ ላይ የተከፈተውን ዘመቻ ምክንያት  በማድረግ ባለፈ ሳምነት በአንድ  መጽሔት  ላይ  ለፃፉት  መጣጥፋቸው በተወሰነ  መልኩ ነገሩ  እንደዚህ  ነው ብዬ እግረ መንገዴን  መልስ ልስጥ፡፡
     ይህ ሰው ከላይ  በገለጽኩት  መልኩ  የሰው  ፍቅር  ያለው  ከሆነና  ለህሊናው የማደር ምልከት  ከሆነ፣ ለህሊናቸው የማያድሩ ሆዳቸውን  ለመሙላት ብቻ  ቆርጠው የተነሱ፣ ሀገር ከኔ ወዲያ ለአሳር የሚሉ፣ታሪክ የሚያጠፉና አርቴፊሻል ታሪክ በእጅ የሚያስዙ፣ በህዝቡ የሚቆምሩ፣ የሀገር አንድነት ስጋታቸው የሆነ፣ ዓላማቸው ገንዘብ መሰብሰብና ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ የሆነ፣ በዜማዎቹ የደቆሳቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቴዎድሮስን  ለማዳከም ሞራሉን ለመንካትና ተቀባይነት ለማሳጠት ቀን ተሌት አይሰሩም አጋጣሚዎችን አይጠቀሙም  ማለት የማይቻል መሆኑ የዘመቻው መሰረታዊ ምክንያት ነው፡፡
  እነዚህ ናቸው እንግዲህ  መልካቸውን  እየቀያየሩ፣ ወንበራቸውን  እየተጠቀሙ  ዜመኛውን ለማንኳሰስ ከዚህ  ቀደም  እንዳንኳሰሷቸውና እንዳንበረከኳቸው  የተለያዩ ሰዎቸ ለማንበርከክ በተለያየ አቅጣጫ አስደናቂ  ድራማ  የሚሰሩት፡፡ አሁን እየተቃረበ ለአለው በ2007 ምርጫ ይህ አርቲስት ወቅታዊ  ሁኔታዎችና መሬት ላይ ያለውን ተጨባች  ሁኔታ  በዜማው  ቀምሮ የመስራት አቅሙን በመጠቀም እርስ  በእርስ  መቆራቆስ  የስራቸው ዋነኛ  ክፍል  ለአደረጉት ተቃዋሚ  የፖለቲካ ፓርቲዎች  የሆነ የሚያግባባ አጀንዳ ይሰጥብናል፣ የሚያደንቀውን ህዝብ አስተውል፣ አትታለል፣ ንቃ፣ አጋጣሚህን  ተጠቀም  ብሎ  አመራር  ይሰጥብናል ብሎ የገዢው  ፓርቲ ቀድሞ የቤት  ሥራውን  እየሰራ ነው ብሎ  መጠርጠርም ጤነኝነት  ነው  እላለው፡፡  እንዲህ አይነት ለክፋት የሰለጠነ ዘመቻ ካለተኬደበት ሌላው  አማራጭ በዓል  ሲቃረብ  ደጋጋሚ የሌቦነት  ልምድ ያላቸውን  ሌቦች ህብረተሰቡ  በዓሉን  በሰላም  እንዲያሰልፍ ከየአሉበት ፖሊስ ሰብስቦ በማሰር  ከበዓል  በኃላ እንደሚለቃቸው፤ የምርጫ  ወቅት ፈታኝ የሆኑ  ሰዎችን ቢያንስ  ምርጫው  እሲኪያልፍ  አንድ  ምክንያት  አደራጅቶ መሰብሰብ  ያስፈልጋል ብሎ  ወደ ዘብጥያ  ካልተጣለ በስተቀር ፡፡

ሲጠቃለል
   ቴዲ አፍሮ ዘፈኑ የማይጥማቸው፣ ለሆዳቸው የሚዘምቱ፣ጥቅማቸውን የሚያሳድድዱ ስለለሀገር መስማት የማይፈልጉ ግለሰቦች ወይም  ቡድኖች ምንም  ጊዜም  ቢሆን መልካቸውን እየቀያየሩ ዘመቻ  ማድረጋቸው  የእህል ውሃቸው ጉዳይ ነው፡፡ ቴዲ  በእነዚህ  ቡድኖች ላይ ጠንካራ መልዕከት ያዘሉ፣ የሚያርዱ ዜማዎች ወይም ስጋት የሚፈጥሩ ዜማዎች ማቀንቀን እስካላቆመ ድረስ በተገኘው  አጋጣሚ እርሱን መታነኮሳቸው የማይቀር  በመሆኑ፤ ቴዲ ለዚህ አይነት  ደካማ ወጥመድ ቦታ ሳይሰጥ የሚጠበቅበትንና የህዝቡን ስሜትን  ተፈጥሮ በለገሰችው  ተሰጥኦ በመጠቀም የበኩሉን አስተዋፆ ማድረግ የእርሱ የህልውና ጉዳይ መሆኑን  ማስገንዘብ እወዳለው፡፡ ብዙ ቴዎድሮሶችም እየተፈጠሩ እንዳለ እንደሚፈጠሩም እያየን ነው፡፡
     እነ በደሌም ሆነ ኮካኮላ አርቲስቱ ተወዳጅነቱን ከግምት በማስገባት በሙዚቃው ስራው የኢትዮጵያን ህዝብን እንደገዛ በመረዳት ምርታችንን በአርቲስቱ ዝና ጥላ  ሥር እናሻሽጥበታለን  ብለው በሚለዮኖች ብር ክፍያ ውል ከተዋዋሉ በኃላ በቂ ባልሆነ ምክንያትውላቸውን ማፍረሰቸው የእርሱን ስሜት፣ ዕውቅናን ለማዳከም የወሰዱት እርምጃ ላለመሆኑ ማሳመኛ አላሳዩንም፡፡ በተጨማሪም የዘማቻው አካል ስላለመሆናቸው ጥያቄ እንጠይቃለን፡፡ በሌላ ማሊያ  እነእርሱው እየተጫወቱ ስላለመሆናቸው እንደ ሰው ካልጠረጠርንም የዋኽ! ልንባል  እንችላለን፡፡
    በዝራው አሻግሬ