ዓርብ 30 ሜይ 2014

ሩቅ አስባ ቅርብ ለማሳደር.........



ሩቅ አስባ ቅርብ ለማሳደር እየተጋች ያለች ሀገር!
                     ግንቦት 20ኢቲቪ

ግንቦት20 1983 ጠንቅቄ አውቀዋለው፡፡ ያን ጊዜ ለአቅም አዳም የደረስኩበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ በተለይ ግንቦት 20 ትዝ የሚለኝ በለጋ ዕድሜዬ አደጋ ውስጥ የገባሁበት አጋጣሚ  ተፈጥሮ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ይሄኔ ይህንን ታሪክ በነፃነት መፃፍ ተረት  ሆኖ ይቀር ነበር፡፡
       ነገሩ እንደዚህ ነው በቴሌቪዥንና በሬድዮ ልክ እንደ የዛሬ ጊዢው መንግሰት አጅሬ የደርግ መንግስትም የሚፈልገውን መልአክት የሚጠላውን ጭራቅ አድርጎ የሚያሳየን፣ የሚያስደምጠን ጊዜ ነበርና፤ እነዚህ ጭራቅ ሻዕቢያና ወያኔዎችን ለማየት ሁላችንም ከፍተኛ ፍላጎት ነበርን፡፡ አስታውሳለው አንድ ከመኖሪያ ቤታችን በቅርብ ርቀት የነበረ ጠጅ ቤት የሚገኝ ጥቁርና  ነጭ ባለሳጥን ቴሌቪዥን ከጠጅ ቤቱ የግቢ በር 20 ሜትር ርቀት ላይ ሆነን ቴሌቪዥን ለማየት ከተሰለፈው ሰው መሀል በመሽለኩለክ፣ በመንጠራራት፣ ከፊት ቁጢጥ በማለት ለማየት ስንሞክር በጣም ትዝ የሚለኝ በዚያን ወቅት በጣም ማታ ማታ በህብረት ትርኢት ፕሮግራም ላይ ተደጋግማ የምትቀርብ የትግርኛ ዘፈን ነበረች፡፡ ድምጻዊዎቹ የትግራይ ተወላጆች ናቸው በካኪ የተሰፋ ቁምጣ፣ እሾህ መከላካያ ገንባሌ፣በረባሶና ሰንደል ጫማ፣ የካኪ ሸሚዝ፣ፀጉራቸው  አፍሮ፣ ወገባቸው ላይ ትጥቅ ያገለደሙ በእጃቸው  ክላሽ የያየዙ ይመስለኛል ቁመታቸው እኩል ቀጠን ያለ ቁመና አላቸው፡፡ አፋቸው ድረስ የመጣውን አንድ በመቆሚያ ላይ ያለ ማይክራፎን በጋራ እየተጋሩ የሽለላ ዘፈን ይመስለኛል(ጊዜውን የሚያስታውስና  ቋንቋውን የሚያውቅ  ሰው በትርጉም ሊያግዘኝ ይችላል) ቁርጺ! ደራራም!....ቁርጺ! ዳራራራም!……..ለወያኔ ምልክቱ  ግንባሩ ላይ መፈንከቱ !(ቁርጺ የምትለዋን ትክክል የሆንኩ  ይመስለኛ ቀሪው ቃል እኔና  አብሮ አደጎቼ ዜማውን በመስማት በተመሳሳይ ቶን ተርጉመን ማታ የሰማነውን ቀን ላይ ስንጫወትበት የተፈጠር ነው፤)ብቻ እንደዚህ ነገር እያሉ በወኔ ሲዘፍኑ፤ ወያኔ ሆነ ሻዕቢያን ጉድጋዱ  ገብተን ድምጥማጣቸውን ልናጠፋ ሸንጦን ነበር! ምን ያደርጋል ለምሳ ስናስባቸው ለቁርስ አደረጉን  እንጂ! ታስታውሱ እንደሆነ ያን ጊዜ በከተማችን የወታደር ጎመኔ ፊሊ ጃኬት እላዩ ላይ  የአሜሪካን ባንድራን ጨምሮ የተለያዩ ባጆችን ለጥፎ ማድረግ ፋሽን ነበር፡፡
     ታዲያ ሻዕባብያና ወያኔዎች ፓስተር አካባቢ ደርሰዋል በአስፓልት ላይ  በሰልፍ  እየሄዱ  ነው ሲባል ከመንደራችን ወደ ዋናው አስፓልት በሚወስደው ቀጭን መንገድ በፍርሃትና በድፍረት መካከል ጥግ ጥግ ይዘን እንደፍራለን የምንል ልጆች ማን ይነካናል እኛ ንጹሁ ሰዎቸን በሚል ማን አለብኝነት ስሜት ወደ ፊት ስንል ከእኛ በእርቀት እታች ግድግዳ ሥር ተደብቀው ከሚያዩን መንደርተኞች የኔን ስም እየጠሩ ይጮሁ ነበር! እኔ ተነጥዬ ወደ አስፓልቱ ልደርስ ትንሽ  ቀርቶኛል፡፡ በዋናው መንገድ ልናያቸው የፈለግናቸው ታንክ  አጅበው ዳር ዳር በሰልፍ ሲሄዱ ያታየኛል፡፡ ስሜን እየጠሩ መንደረተኞቹ ይጮሃሉ፡፡ ሰልፈኞቹ ሲያልፉ ከመሃላቸው  መሳሪያ ደግነው ሰው  በሚገፈልግ  መልኩ ወደ መንደራችን  ማስገቢያ  እንደመግባት እያሉ በመመለስ መንገዳቸውን ይቀጥላሉ የመንደር ውስጥ የመሸገ ወታደር ካለ የሚያጣሩ ነው የሚመስለው፡፡ አንዲት ሴት ተጋዳላይ መሳሪያዋን ወደ እኔ አቅጣጭ ስትደግን እና ፊሊ ጃኬትህን  አውልቅ ! ፊሊጃኬት!  አለቀልህ! አውልቅ! እየጮኹ ሲሉኝ ለካስ ፋሽን ያልኩት ፊሌ ጃኬት ነው ያደረኩት! አለቀልኝ መንደር ውስጥ የተወሸቀ የደርግ ወታደር መስያቸው ሊፋለሙኝ ነው፡፡ በድንጋጤ በሰከንድ ላብ በላብ ሆንኩና ተንደርድሬ አጠገቤ መለስ  የተደረገ የቆርቆሮ በርን  በርግጄ  ገባው፡፡  አንድ ተጋዳላያ ወደ መንደሩ ትንሸ ገባ ለማለት  ሞክራ ወደ  ኃላ  በመመለስ ሄደች  አሉኝ፡፡ ያን ጊዜ ሟች እንደነበርኩ ያረጋገጥኩት ከሳምንት  በኃላ የሰፈራችን  አንዲት ሴት የአንድ ዓመት ህጻን ልጇን በጀርባዋ አዝላ ጋዝ  ልትገዛ ነዳጅ ማደያ ሄዳ ግርግር  ሲነሳ ልትሮጥ ስትል ጫማዋ ወልቆ ጫማዋን ልታነሳ ጎንበስ ስትል ሴት ታጋይ ናት አሉ  አነጣጥራ ተኩሳባት መሞቷን በስሰማው ጊዜ ነው፡፡ ዛሬ ልጇ  አድጐ፤ ሴትየዋም  ከሞተች 23 ዓመት ሊሆናት ነው፡፡ ምን አለ አቲቪ አንዲት ወጣትን እየሳየ የሚያሳየው የግንቦት 20 ማስታወቂያ ላይ ሚዛናዊ  ለመሆን ይህ ልጅንም ስለግንቦት 20 የሆነ ነገር  እንዲል ከጎን ቢያቀርቡት አልኩ  በሆዴ፡፡
     ታዲያ ግንቦት 20 እንዴት አላስታውስ አስታውሰዋለው እንጂ! የሰይጣን  ጆሮ አይስማና  የግንቦት ሃያን የሚያስጎመጅ ውጤት ለኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን፣ መሠረተ ፓርቲ ሚዲያዎችና እና ለአጋር የሚዲያ ድርጅቶቹ ልተውና እነሱ ባልሄዱበት  መንገድ ወይም ሊያነሱት የማይፈልጉትን የግንቦት 20 ፈተናዎችን ለማስታወስ ልሞክር፡፡ ልማታዊ ጹህፍ ለምን አልጻፍክም እንደማልባል አርግጠኛ ነኝ ምክንያቱም ግንቦት ሃያ ያቀዳጀኝ ሀሳብን  በነፃነት የመግለጽ መብቴን ነው የተጠቀምኩት፡፡ ደሞም መንግስትን እንከን  የለሽ  አድርገው ወይም የመንግስትን ችግር ለመሸፈን ሰርክ ከሚለፉፉት የመንግሰትና መንግስት ቀመስ መገናኛ ብዙኃኖች ይህ መንግስት ሲቀየር የቀድሞው መንግሰት የሠራቸው አስከፊ ተግባሮች ብለው ወደፊት ፕሮግራም አስኪሰሩ ድረስ እነሱ የመንግስትን አሪፍ ሥራ ሲለፍፉ እኛ ደግሞ ችግሮቹን እየገለጽን የጋዜጠኝንነትን መርህ ለመጠበቅ ባላንስ እንዲሆን እኛ የዜግነታችንን እንክፈል፡፡ ወደ ገደለው ልግባ፡፡
   ትውስታ-1 የደርግ ወታደር  
1983 ስናስብ በአፍሪካ ተወዳደሪ የለውም የሚባለው የደርግ የወታደር ኃይል መበታተን የወታደር መለዮ የለበሱ ሰዎች አደባባይ ላይ ወጥተው አገሪቷ ያላትን የለማኝ ቁጥር  በከፍተኛ ደረጃ እንዲያሻቅብ ያደረጉበት አጋጣሚ የሚታወስ ነው፡፡ ወታደሮቹ የኢትዮጵያ ወታደር ሁሉ  አይመስሉም፡፡  በየቦታው እንደ ጨው ዘር  ተበትነዋል፡፡ የአይዶሎጂ ችግር አለ እንኳን አለ ቢባል ተሃድሶ ተብሎ ተዘግይቶ እንደተሞከረው ይህ በኢትየጵያ ህዝብ አንጡረ ሀብት የሠለጠነ የኢትዮጵያ ሰራዊት አመለካከቱን እንዲያስተካክል በቂ ሥልጠና ሰጥቶ መጠቀም ሲቻል መበተኑ ገራሚ  ትውስታ ነበር፡፡
ትውስታ-2 የሸጎሌ ቃጠሎ
ሁኔታው እስኪረጋጋ ብለን ትምህርታችንን አቋርጠን በየበራችን በመቆም ሁኔታውን ስንከታተል  በጭንቅላታችን ላይ የጦር አውሮፕላን ለጣራ  ቀርቦ እየተምዘገዘገ እንደሁነ አይነት  ከፍተኛ ድምጽ ሰምተን መሬቱ ሲንቀጠቀጥ ጭንቅላታችንን መሬት እየቀበርን ባለንበት  ለመደበቅ  ሞከርን፡፡ ኋላ ላይ ስንሰማ ሸጎሌ ያለው የመሳሪያ ካምፕ ግርግሩን በመጠቀም መንደርተኛውም ሆነ ከርቀት የመጣ ህዝብ ሰዉ ዕቃ እየወሰደ ነው በማለት የሚረባም የማይረባም ዕቃ  በቻሉት መጠን ሲወስዱ በአየር ላይ የሆነ ነገር ወድቆ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ ተሰምቶ ነው የሚሉት አካባቢውን ሬሳ በሬሳ ያአደረገው፡፡ ያን ጊዜ የአክስቴ ልጅ  እንደ ከሰል የደረቀ ሬሳ የአጥር ሽቦ ሳይቀር ይዞት ከሰል መስሎ ተገትሯል እንይ ብለውት ከጋደኞቹ ጋር ሄደና ሬሳ አይቶ ከመጣ በኃላ ጤና አጣ፣ መቃዠት  ጀመረና ምን እንደነካው ሳይታወቅ ሞተ፡፡
ትውስታ-3 ኢትዮ ኤሪትራ
1992 የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትም ለግንቦት ሃያ የሚነሳ  ጉዳይ  ነው፡፡  ኤርትራ ኢትዮጵያን ልትወር  ነው ተባለና  “ከማይረባ  ሽሮ  ይሻላል ሽራሮበማለት ይህ ወጣት ተነሳ፣ ሽማግሌም  ሳይቀር ተነስቶ፣ የተረሳ የደርግ ወታደርም ተፈልጎ  ቀይባህርን ወስዳ አንጀታችንን  ያሳረችንን ኤርትራን ለመበቀል ህዝቡ ጠቅልሎ ተነሳ!  በስንት  ሺህ  የሚቆጠር ህዝብ  ከወንድሙ ጋር በመታኮስ ህይወቱን አጣ፡፡ አስታውሳለው የወ/ አስካለች የልጅ ልጅ አብዮት 8  ክፍል ሲያስቸግረው ትምህርቱን አቃርጦ መንገድ  ዳር ሠፈር ውስጥ እየተቀመጠ እንደ ድሮ ቢሆን ወታደርነት ይቀጠራል አሁን ምን ልሁን  ብሎ ተቸግሮ ነበርና ይህንን አጋጣሚ ሲያገኝ ባድሜን አያርገኝ ብሎ በስውር ጦርነቱን ተቀላቀለን ኋላ ላይ ስንሰማ  ሁለት  እግሮቹ  በፈንጅ  ተቆረጡ ተባለና  ሆስፒታል ጦር ሃይሎች  ገባ፡፡ እዛ ጦር ኃይሎች ውስጥ  ጦርነቱ  ካበቃም  ወዲህ  ተቀምጦ ነበርና አገግምሃል ውጣ ሲሉት እግር የለንኝም የት  ሊሂድ ብሎ ዘራፍ  በማለት ወደ ሚኪሊላንድ ማቆያ ተወሰደ፡፡ በስተመጨረሻ ልጁ ብልጥ ነው ቤት ሁሉ  ተሰጥቶታል  ነው የሚባለው! ግን  ምንያህል ወንድሞቻችን  እንዳለቁ መግለጽ ለቀባሪው  አረዱት  ነው፡፡
ትውስታ-4 ብሔርተኝነትና  ጎሰኝነት
ይሄም  የግንቦት  ሃያ ፍሬ  ነው፡፡  በፊት  ልጅ  ብንሆንም ብሄር  ምንድን  ነው? ማነው? የሚለን  ሰው  የሌለ  ወይም  እምብዛም  አንደማይታወቅ አስታውሳለው፡፡  ይህ  ማለት  ብሔረሰቦች የሉም ማለት አይደለም፤ እንዲሁም መስከረም ሁለት  ልክ እንደ ዛሬው የብሔረሰብ  ቀን ሲከበር እንደሚታዩት ብሔር ብሔረሰቦች  የአብዮት በዓል ቀን ማክበር እየተባለ እኛ  የከተማ ልጆቸ የማናቃቸው ብሔረሰቦች ሁሉ በቴሌቪዥን አብዮት አደባባይ ሲጨፍሩ  አይተናል፡፡ የግንቦቱ ብሔረሰብ ግን አስገዳጅነት  ያለው  ሁሉ ይመስላል፤ ሂደቱ የሚጀምረው መታወቂያ  ላይ  የብሔርን ስም እንዲገለጽ  በማድረግ  ነው፡፡  ሲቀጥልም ስብሰባ ልትሰበሰብ፣  ሥራ ልትገባ ብቻ የሆነ ፎርም መሙላት ሲገባህ ብሔር መጠየቅህ የግድ ነው፡፡  ኢትዮጰያዊነት የማቀጨጭ ዘመቻ ይመስላል፡፡ በብሔር ተደራጅ  ተብለህ  እንኳን ወደ ኃላ የማለት ሁኔታ  ካሳየህ አንተ  ፀረ-ብሔር  ተብለህ ላለመፈረጀህ ዋሰትና የለህም፡፡ ግን ኢትዮጵያዊቴን የሚያጠፋ ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ ከጊዜ በኃላ ጋደኝነት የመሰረትን በጎሳ የተቃኘ አንድ ሰው አንድ የመዝናኛ ስፍራ እየተዝናናን ሳለ የእኔ ብሔር  ዘፈን  ለምን  አልተዘፈነምዲጄው ይክፈት እያለ ሲጮኽ  እበካህ ተወው አሁን  እየተጫወተ ያለው ዘፈን ሁሉንም ሰው  ይወክላል ከታገስክ  ደግሞ የአንተ ብሔር ዜማም  ይሰማል፣ አይን  ውስጥ አትግባ  ስለው  አንተ  ብሔርተኛ  ነህ  አለኝገርሞኝ አኔ አዲስ  አበባ  ተወልጄ ያደኩ ብሔሬ  ኢትዮጵያዊ የሆነ እነዴት  ከኔ  ጋር የማይሄድ  ያነሳል ብዬ፤ እንዴት? ስለው  ኢትዮጵያዊ  ብሔርተኝነት  አለብህ  አለኝ፡፡ እውነቱን  ነውግን  ለመጀመሪያ  ጊዜ  ኢትዮጵያዊ  ብሔርተኝነት የሚባል  መኖሩን  ስሰማ፡፡ የኔ ስጋቴ ለነገሩ  ከመገመት ውጪ ብሔሬ ምን እንደሆነ አያውቅም እንጂ የመሰለኝ ግን የኔን ብሔርን በማንሳት ጎጠኛ፣ ጠባብ ነህ ይለኛል ብዬ ነበር በስጋት  እከታተለው  የነበረው፡፡ ታዲያ ከዚህ ሰው ጋር ያን ዕለት ተጋጨችን፡፡ አድርገን የማናቀውን የየራሳችንን  ሂሳብ  ከፍለን ተጣልተን ተለያየን! ተለያየን!
        ትውስታ -6  የውሃ፣የመብራት የስልክ በመቋረጥ
የግንቦት 20 ሌላው ቁልፍ  ተውስታ መብራትና ውሃ ለረጅም ጊዜ መጥፋት፣ በተራ  መብራት ማግኘት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መብራት  ከተጀመረ በኃላ  በታሪክ ተከስቷል  የማይባለው በጨለማ ውስጥ መኖር፣ በውሃ ዳር ተቀምጦ ውሃ ፍለጋ በኪሎ ሜትር  መጓዝ፣ የኩራዝ፣ የሻማ ተጠቃሚ  መሆን፣ የጄኒሬተር  ጩኽት  በየንግድ ተቋሙ  መስማት፣ ስልክ  መቋረጥ፤ የዚህ  ዘመን  መለያው ከማለት ወጪ ምን ሊባል  ይቻላል!! እንደ  ክፉ ቤት  አከራይ  በሠላም የተቀመጠ ህዝብ ላይ መብራት ማጥፋት፣ ውሃ  ማጥፋት፣ ስልክ  ማቋረጥ የልማተዊ እንቅስቃሴው ወይም የእድገት  ምልክት  ነው  ከተባለ!! አሁን!... አሁሁን  እንኳን! ይህንን ጹህፍ እያዘጋጀው  በግንቦት 20 ዋዜማ መብራትና ውሃ ጠፍቶ፤ እረ እባካችሁ እዚህ አካባቢ ውሃ፣ መብራት እያለን ጮኽን ጮኽን ድምፃችን ሲሰልል ደስ ያላቸው  ጊዜ ይልቀቁት ብለን ተቀምጠናል፡፡
ትውስታ-7 ፎረም/መደራጀትና ግዴታ
ይህች ፎረም  የሚላትም  ቋንቋ  የግንቦት ሌላው ገፅታ ናት፡፡ መጀመሪያ ጊዜ የወጣት  ፎረም  በማለት  ነው  የተጀመረው  አሁን  ግን  ተለጥጦ፣ ተለጥጦ የነዋሪ  ፎረም  የሚልም የሰማው  መሰለኝ፡፡  ፎረም የአንግሊዘኛው FORUM በአማርኛው መድረክ የሚለውን  ትረጉም የሚሰጥ  ነው፡፡  የእኛ ችገር የቃላት አይደለም፡፡ ፎረም ነኝ፣ ነው በማለት ፎረም ያልሆነ ኢትዮጵያዊን ከኢትዮጵያ  ሪሶርስ  እንዳይጠቀም  ገለልተኛ ማድረጉ ላይ ነው፡፡  እርግጥ  ነው ፎረም ይባል፣ ማህበር  ይባል የማህበሩ  አባላት ሁሉ  ተጠቃሚ  ናቸው  ማለት  አይደለም የፈጠኑ  አፈጮሌዎች ግን  አይጠቀሙም  ብሎ ማሰብ የዋኽነት  ነው፡፡  በፎረም ስም  ድሮ የምናቃቸው  የስልጣን  ኮርቻ ላይ ፊጥ ብለው በሌላ  ማሊያ  የሚጫወቱ  ከሆነም እንኳን ባለ ህንጻ ቢሆኑ አይደንቅህም! ፎረም ላይ  ናቸው መቼ ሰርተው ነው ብለህ መጠየቅ  አሁንም  ፋራ ያስብልሃል ወይም ያሰበላሃል፡፡ ህሊና፣ ግብረገብ፣ነውር፣ግፍ ነው፣ ጂኒ ጃንካ..  ቁልቃል.. የምትል ከሆነ ፎረምም ብትገባ ቁልቁል  ነው የምትወርደው፡፡የሚገርመው አንዳንዴ ይሄ  ማህበር ነጻ ማህበር ነው መንግስት ድጋፍ ያደርግለታል እንጂ ነፃ ነው ትባላለህል፡፡  አይደለም  ልትል  አትችልም  ምክንያቱም  እጅህ  ላይ  ማስረጃ  የለማ ወይም አንተ  ማስረጃ  ልትሆን  አትችልማ! ነጻ አባል የለም  እያልኩ አይደለም  አለ  ግን እሱ  ከጀርባው  የሚሰራውን የማያቅ ይሆናል፡፡   አነሰ ቢባል  በቀጥታም ይሁን  በተዘዋዋሪ  የማህበሩ ይሁን  የፎረሙ  ወሳኝ  ሰዎች እነሱው  ናቸው፡፡ ከደርግ አኢወማ፣ አኢሴማ  መፋታት  አለባቸው እየተመጋገቡ መጓዝ አይቻልም! እስቲ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበርን በምህጻረ ቃል  እንየው(አአወማ) የተቀራረበ አልመስላችሁም? የአዲስ አበባ ሴቶች ማህበርስ(አአሴማ) ይሄም አኢሴማ አይነት ቶን አለው አብዮታዊ ኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር ፡፡
ትውስታ -8  ልማታዊ ሌባ
በዚህች ዘመን የማናልፋት ጉዳይ ቢኖር ልማታዊ ሌባ መብዛቱ ነው፡፡ ልማታዊ ሌባ  ከመንግስት  ባለሥልጣን ይጀምራል፡፡ ነብሳቸውን ይማርና ቆራጡ  መሪያችን  እኮ የመንግስት  ሌቦች  አሰቸገሩን  ብለው  አምረው ነበር፡፡ ታዲያ የመንግስትና  የግል ሌቦች ተደራጅተው ወይም  ተቀናጅተው ሲፈልጉ ሲሸላለሙ ሲፈልጉ ሲያፈናቅሉ  ሲፈልጉ የባንክ  ቤት  ገንዘብን አንደራሳቸው ሲያዙበት፣ ሲፈልጉ ደግሞ ብረት  ወርቅ ነው እያሉ ሲቆምሩ፣ ሲያሻቸው ደግሞ የዘረፋ ፕሮጀክት  እየነደፉ ለመንግስት አጋራ ሌቦቻቸው  ፈርቅ  እየያዙ በዚህ  ጭቁን  ብሶት የወለደው ህዝብ ኑሮ ላይ ውሃ ይቸልሳሉ(እሳት ብቻ እንዳይቸልሱ ጸሎት እናደርጋለን)፡፡ በቡድን ስም የሚቃቀሙትን ካምፓኒዎች ለጊዜው ልለፋቸው ከቀይ መስመር እናዳላልፍ! ብቻ እነዚህም ከግንቦት 20 ጋር አብረው በየመ/ቤቱ ወይም  በየቀበሌው አዳራሽ አሊያም በየመንደር ጎጥ  ቡና ላይ ጎን ለጎን ይከበርልን፡፡  
ትውስታ-9 አባልነት ለሥራ ማግኘትና ለዕድገት
አባል ሁን ሥራ እንድታገኝ፣ ዕድገት እንድታገኝ፣ ስልጣን እንድታገኝ  የሚል ጉትጎተና  ምልመላ ከመንደር እሰከ መንግሰት መሥረያ ቤት እስከ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ምልመላ፤ የተጣጧጧፈበት ጊዜ፡፡
ትውስታ -10  ምርጫ 1997
ግንቦት  1983 በኃላ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች  የእውነትና የውሸት  ሲሳተፉ  በኢትዮጵያ ታሪክ ያየንበት ቢሆንም 1997  ለየት  ያደርጋታል፡፡ የመንግስትንም ግራ የሚያጋባ ባህሪ  ወደ  እውነተኛ  ማንነቱ  እንዲመጣ  የተገደደበት  ጊዜ  ነበር፡፡  ይገርማችሁል ከዚህ  በፊት  ረብሻ ተነሳ  አልተነሳ ብዙ  ጉዳዬ አልነበረም፡፡ 1997 . ግን ሰዎቸ  ወደ  አውሬነት  ሲቀየሩ ለአዛውንት፣ ለህጻናት፣ ለሴቶች ፣ለሃይማኖት መሪዎች፣ክብር ሲነሳ ጥይት እንደ ውሃ  ሲረጭ፣ መግቢያ፣ መሸሸጊያ  ሲጠፋ፣ ቤተክርስቲያን መስጂድ ጠለላ መሆን  ያልቻሉበት ፣የሰው በር እየተሰበረ ሲገባበት አጠገባቸው ሆነን በአይናችን የአየንበት ጊዜ ነው፡፡ ሰዎች ተለቃቅመው ያለዕድሜ ያለፆታ ፣ያለማህበረዊ ከበሬታ ወህይኒ ቤት ሲወረወሩ  ህገመንግስታዊ ሥርዓቱን በሃይል  መናድ፣ አገር  ክህደት፣ የሚሉ ወንጀሎች  ለአገራችን የተወዋወቅንበት  ጊዜ ነው፡፡
ትውስታ -11 ሙስና
ቀደም  ባለው መንግስት  ያለአግባብ በገንዘብ ፣በማቴሪያልና  በዝምድና ከህግ  ወይም  ከአሰራር  ውጪ ሲሰራ ጉቦ ተቀብሎ ነው  ወይም  ተቀብላ  ነው  ሲባል  ሰምተናል፡፡ ዛሬ ጉቦ ወደ ሙስና አድጋ ወይም  ተላልፋ  ሙስና  እንደ ኬኒያ የተለመደ  ተግባር ሊሆን ጥቂት  የቀረበት ጊዜ፣ ስለሙስና በቴሌቪዥን  መግለጫ  የሚሠጡ ታላላቅ ሰዎች  ከመጋረጃው  ጀርባ በሀገር እያሳይዙ ሙስና ሲጫወቱ፣ አይን አፍጥጠው ገንዘብ ሲጠይቁ፣ ሲያሰጠይቁ ያስተዋልነበት ዘመን ነው፡፡
ትውስታ -12 ሽብርተኛናትና እስራት
ሽብርተኛነትና ጋዜጠኛነት፣ ሽብረተኛነትና የመብት ጥያቄ አንሺነት፣ ሽብርተኛነትና የፀረ-ሽብር ህግ ፣ሽብረተኛነትና ተቃዋሚ፤ ዞሮ ዞሮ እስራት በሀገራችን ታሪከ ለመጀመሪያ ጊዜ  የተዋወቅንበት ሁኔታ ከግንቦት 1983 በኃላ ነው፡፡
ሲጠቃለል
ግንቦት  20  ከኢቲቪና ከአጋር ሚዲያዎች በተለየ መልኩ የምናስታውስበት 101 ክስተቶች እስከ ዝርዝራቸው አሉን፡፡ ቢሆንም የግንቦት 20 ችግርቹን አታሳዩን ለምትሉ እናንተም የእናንተ አሰልቺ ፕሮፓጋንዳችሁን ከፊታችን አጥፉ ከጆራችን አርቁ፡፡ የሚዘገንኑን፣ የሚያሳዝኑን፣የሚያስከፉን፣የሚያስፈሩን፣የሚያሰቅቁን፣ያጎሳቀሉን፣ያራቆቱን፣ያሰራቡን፣የበይ ተመልካች ያደረጉን፣የገደሉን፣ ሩቅ አሳቢ  ቅርብ  አዳሪ ያደረጉን ህመሞቻችን  አሉና!  
በዝራው አሻግሬ




ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ