መንበር
ናፋቂ ከያኒዎች!
ክፍል-፩
ኪነጥበብ ብለን በርካታ የኪነጥበብ ግብአቶችን እያነሳን ቲያትር፣
ፊልም፣ ሙዚቃ እያልን ልንጠቅስ እንችላለን፡፡ የኪነጥበብ ግብአቶች እያልኩ ለመዘርዘር አምሮኝ ሳይሆን በአገራችን ውስጥ
ኪነጥበብን ራቅ ብለው በንጹህ ህሊና ሲያስተውሉት ምን ሁኔታ ላይ
ነው ያለው የሚለው መጠነኛ ትዝብቴን ለማሳየት ዳድቶኝ እንጂ! ስለ ከያኒዎች ልናወራ ስለሆነ ለግንዛቤ ይረዳን ዘንድ ከያኒ ወይም ህጉ ከዋኝ በማለት በቅጅና ተዛማች መብቶች ጥበቃ አዋጅ
ቁጥር 410 ላይ የሠጠውን ትርጉም
እንይ፡-
አንቀጥጽ 19
ከዋኝ ማለት ተዋናይ፣ ዘፋኝ፣ ዘማሪ፣ ሙዚቀኛ፣ ተወዛዋዥ፣ እና ሌላ
ማንኛውም የሚተውን፣ የሚያወጣ፣ የሚጫወት፣የሚዘፍን፣ የሚያዝናና ወይም
በሌላ ማናቸውም አኳኃን የሥነጽፍና የኪነጥበብ ሥራን
የሚከውን ግለሰብ ነው፡፡
እስቲ ከሙዚቃ ልጀምር ሙዚቃ የአለም ቁንቋ ነው የሙዚቃ ዜማው፣
ግጥሙ ብዙ ያናግራል፡፡ ሙዚቃ በአለም ላይ ሰዎች ተግባብተውበታል፣ ከእንቅልፋቸው ነቅተውበታል፣ በፍቅር ወድቀውበታል፣ ተቃቅፈው
ተላቅሰውለታል፣ መሳሪያ ጥለው ተሳስመውበታል፣ ሰላም ዘርተውበታል፤( እዚህ ጋር ቦብ ማረሌይ የደቡብ አፍረካ ተቀናቃኞችን አፓርታይድ ሲገረሰስ ዋን ላቭ
በሚል ዜማው ያስተቃቀፈበትን ቅጽበት ማንሳት ይቻላል አገራችን ላይም የህዙብን ችግር በማንሳት፣ በማጽናናት፣ በድፍረት በመገሰጽ
ቀላል የማይባል ስራ ሰርተው ህዝቡ ልብ ውስጥ የነገሱ ከያኒዎችን ማንሳት እንችላለን
አርቲስት ጥላሁን ገሰገሰ፣ አርቲስት ቲዎድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ)፣አርቲስት እጅጋየው ሽባባው፣ አርቲስት፣አርቲስት ኪሮስ አለማየው፣
አርቲስት አስናቀ ገ/የስ፣ አርቲስት አብዱ ኪያር፣ ወዘተ… ጥቂቶቹ ናቸው፤)በአንፃሩ ይግሞ በሙዚቃ ሰዎች ጥላቻ ነዝተውበታል
ርካሽ ተወዳጅነት አትርፈውበታል፣ ገንዘብ ሰርተውበታል; ብዙ ማለት ይቻላል፡፡
አሁን አሁን በአገራችን ያለውን የሙዚቃ ሂደት ስናይ የሆነ
ግርምታ
ይጨርብናል፡፡ ዘፋኞች በአሁን ጊዜ ምን እያሉ ነው የሚዘፍኑት ሁኔታቸው ምን ይመስላል ብለን ብናስተውል
ብዙ ደስ የማይል ድባብ ልናይ እንችላለን፡፡እንደ እኔ አስተሳሰብ ሙዚቃ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መዋል አለበት ብዬ አስባለሁ፤
ህብረተሰቡን ለሚጠቅሙ ጉዳዩች መዋል አለበት የሚለው ሐሳብ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ሙዚቃ ህብረተሰቡ ሲያለቅስ አብራ ማልቀስ፣
ህብረተሰቡ ግራ ሲጋባ ሙዚቃ መንገድ ልታሳይ ተስፋ ልትፈነጥቅ ይገባል፤አለበለዚያ ህብረተሰቡ እያለቀሰ ደረት ሲደቃ ዳንኪራ
የምትደልቅ፣ ህብረተሰቡ ሲጨነቅ ሲሰቃይ በፌሽታ የምትፈነጥዝ እና ህብረተሱቡ ጭንቅ ላይ ሲሆን ግራ ሲጋባ ከፊት ሆና ያልመራች
መንገድ ያላሳየች ሙዚቃ የህብረተሰቡ ሳትሆን እሷ የእነርሱ ናት፡፡
አገራችን ውስጥ ያሉ ሙዚቃዎች ወይም ሙዚቀኞችን ስናይ ቁጥራቸው
ቀላል የማይባሉ አርቲስቶች ቢዝነስ ተኮር ህሌናዊነት የሚያንሰው፣ከአንጀት ያልሆነ የአንገት ሙዚቃ ሲሰሩ አስታውለናል፡፡
ከአንዳንድ ሙዚቀኞች ጋር ለመነጋገር እንደሞከርኩት አንድ ነጠላ ዜማ መስራት አለብኝ ብሎ አንድ ዘፋኝ ሲነሳ ለህብረተሰቡ
ጠቀሜታውንና ደረጃውን ከግምት በማስገባት ብቻ ሳይሆን በሬድዮ ሊለቀቅልኝ፣ ክሊኘ ካለው በቴሌቪዥን ሊታይልኝ ይችላል ወይ ነው
የመጀመሪያው ጥያቄ!! ስለ እገሌ ብሔር እንደ እነ እከሌ ብሰራ እውቅና አተርፋለሁ ከድህነት ማጥ ውስጥ ተፈትልኬ እወጣለሁ ነው
ህልሙ፡፡ ከድህነት መልካም ስራ ሰርቶ መውጣት መጥፎ አይደለም ችግሩ ርካሽ ተወዳጅነት ለማትረፍ መስራቱ እንጂ፡፡
በአገራችን
አሁን፤ አሁን የሚታየው ነጠላ ዜማዎች ወይም በየአልበሙ ጣል የሚደረጉ አንድ ሁለት ዜማዎች በተራ ስሌት የተሰሩ ናቸው ለማለት
ያስቸግራል፡፡ በተለይ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችን ማዕከል አድርገው የሚሰሩት ዘፈኖች በዋዛ ፈዛዛ የተሰሩ ናቸው ማለት
ያስቸግራል፡
እነዚህ
ዘፈኖች የሙዚቃ ቅንብራቸው ብዙ የሚያስከፋ ላይሆን ይችላል ችግሩ ግን ሙዚቃዎቹ ምንን ታሳቢ አድርገው ነው የተሰሩት ነው
ጥያቄው፡፡ በእኔ ግምገማ ሙዚቃዎቹ የሚሰሩት፡ -
1ኛ) እነ እከሌ ስለ ሰሩ እኔ ብሰራ ያዋጣኛል፤
2ኛ)
የብሔር ብሔረሰብ ጉዳይ ስለሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የመንግስት መገናኛ ብዙሐን ወይም ከመንግስት ተፅእኖ
ያልተላቀቁ የግል መገናኛ ብዙሐኖች ዜማዬን ደጋግመው በማስደመጥ ወደ እውቅናው አለም ይቀላቅሉኛል፤
3ኛ) መሬት
ሊሰጠኝ ወይም ደግሞ የተለያየ ምክንያተ እየተሰጣቸው በብሔር ብሔረሰቦች ስም የሚዘጋጁ የመንግስት ዝግጅቶች ላይ እጋበዛለሁ
የሚሉት ምክንያቶች ዋነኞች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
በነገራችን ላይ ሙዚቀኞች ብቻ አይደሉም ይህንን ስሌት በመስራት
የሚንቀሳቀሱት ፊልም ሰሪዎች፣ ተዋናዮች፣ ሰዓሊዎች፣ ሬድዮ ኘሮግራም አዘጋጆች፣ ደራሲዎች ወዘተ በማለት ከተግባራቸው በመነሳት
አሁን እያዘጋጁት ያሉት ኘሮጀክት ከላይ የጠቀስኩት ስሌት መነሻ ወይም እንደየዘርፉ ባህሪ ይህን መሰል ስሌት ይዞ ነው ፡፡
የአዲስ
አበባ ከተማ መስተዳድር ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በሚያዘጋጀው አዲስ ዝክረ ነገር የሚል ርዕስ ያለው የቴሌቨዥን ቶክ ሾው ላይ
የኪነጥበብ ፋይዳና
የመንግስት ድጋፍ ላይ የውይይት ፕሮግራም በሰሜን ሆቴል ያዘጋጀው ፕሮግራም ላይ
ተገኝቼ በጉዳዩ ላይ አስተያየቴን እንድስነዝር ተጋበዝኩኝ፤ የዛሬ
አነሳሴ ስለ ዝግጅቱ ላወራ አይደለም እዛ ያየሁትን የታዳሚዎች
አስተሳሰብ አሁን ካነሳሁት ጉዳይ ጋር አያይዤ ላወጋችሁ እንጂ! ታዳሚዎቹ
ከተለያየ መ/ቤት የመጡ ናቸው፤ ከቲያትር ቤቶች፣ ከአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ፣ከደራሲያን ማህበር፣ ከተዋንያን ማህበር፣ ከሙዚቀኞች
ማህበር ወዘተ እንዲሁም ከተለያየ የኤሌክትሮኒክስ እና የህትመት ሚዲያዎች እና የተለያዩ ግለሰቦችም የተጋበዙበት ነው፡፡ በዚህ
ወቅት ቲያትርቤቶች እና ትያትረኞች ልማታዊ ስራ መስራት አለባችሁ እየተባለ ዘመቻ
የሚደረግበት ወቅት ነበር፡፡በዚህ አጋጣሚ በሀገርፍቅር ቲያትር ቤት በእዚህ መሰል ስብሰባ ላይ የተሳተፈ አንድ ባልንጀራዬ ከመድረክ መሪዎች
አንዱ አለ ያውን እዚህጋ ባስገባ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ተናጋሪው ቁጭ ብላችሁ በሳምንት አንድ ቲያትር እየሰራችሁ የመንግስት ደመወዝ በመብላት የራሳችሁን ቢዝነስ ታሯሩጣላችሁ አለ ብሎ
አወጋኝ፡፡ በርግጥ ተናጋሪው የገለፀው ትክክል ነው ሀሰት ነው ማለት አይቻልም፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኪነጥበበኞች ቲያትር
ቤቱን እንደ የጡረታ ደመወዝ የመቀበያ ቦታ አይነት አድርገው ነው የሚወሰዱት ማለት ይቻላል፡፡ ፊርማ ይፈርማሉ የራሳቸውን ስራ
ወጣ ብለው ሲያሯሩጡ ቆይተው ይመለሳሉ፤ ለመሯሯጥ አቅሙ እና አጋጣሚው የሌላቸው ደግሞ ይህንን ፊልም ወይም ወይም ይህንን ድራማ
ስሩልን የሚል ሰው እስኪመጣ እንደ ጡረተኛ ቲያትር ቤቱ ቁጭ ብለው ነው፡፡ አንዳንዶቹ ይህንን ክፍተታቸውን ለመሙላት የአባልነት
ፎርም ሞልተው በተወሰነ ነፃነታቸውን አውጀዋል(የሚገርመው ጡረታ ሊወጡ ጥቂት ግዜ የቀራቸውም ነጭ ጸጉር ያበቀሉ አርቲስቶችም
ቀጣዩ ዘመን የእነርሱ እንዲሆን ወደ ጎራው መቀላቀላቸው አስደንቆኛል)፡፡ለዚህ መፍትሄ ምን ተቀምጧል? የማን ችግር ነው? የሚል
ጥያቄ ሊነሳ ቢችልም አሁን የተነሳሁበት ርዕሰ ጉዳይ ስላልሆነ ወደ ጉዳዬ ቀጥታ ልግባ፡፡ በቲያትር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተናጋሪው
ተናገረ ከተባለው የገረመኝን ላስከትል፤ በቀድሞ ዘመን ቢሆን የኪነጥበበ ባለሙያ
ወደደም ጠላም አንድ አብዩታዊ ስራ ይሰራል!! እኛ ይሄ ጠፍቶን ነው እንዴ?! አሁንስ አላበዛችሁም?! እስቲ ልማታዊ ቲያትርና
ሙዚቃ ሰርተናል ብላችሁ እየቆጠራችሁ አሳዩኝ በማለት ከአሁን በኋላ ልማታዊ ስራ ብቻ መስራት የወቅቱ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ተረግጦ
የተነገራቸው ስለመሆኑ አወጋኝ፡፡
የሰሜን ሆቴሉ ኪነጥበብ አስተዋፅኦና የመንግስት ድጋፍ ወደሚለው ስብሰባ
ልመለስ፤ከላይ እንደገለፅኩት የተለያዩ ግለሰቦችና የመስሪያ ቤት ተወካዬች ታድመዋል፤ለጆሮአችን አዲስ ያልሆኑ ስሞችን መጥቀስ
እችላለሁ፡- ሙሉ ገበየሁ፣ ደበሽ ተመስገን፣ ጌታቸው በለጠ፣ ዳዊት ይፍሩ፣ ነብዩ ባዬ ከታዳሚዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ከዚህ ቦታ ላይ የውይይቱን ድባብ ወጣ ብለን በትዝብት ብናስተውል የአገራችን
ኪነጥበብና ኪነጥበበኞች ወዴት እያመሩ እንደሆነ አህምሮአችን ላይ ስዕል የሚከስት ይመስለኛል፡፡እኔበዚህ ስብሰባ ላይ የተገኙ
ተሰብሳቢዎችን በሶስት ጐራ ከፍዬ ማሳየት እችላለሁ፡-
1ኛ) እነ ሙሉ ገበየሁን
እና መሰሎቻቸው ኪነጥበብ ለአገር የሚገባትን አልሰራችም (ለአገር ሲባል ለገዢው መንግስት የሚሉ ይመስላል) የየራሳችንን
ኪስማድለቢያ መንገድ ነው ስንነድፍ የነበረው የሚሉ፤
2ኛ) እነ ጌታቸው በለጠ ኪነጥበብ የምትችለውን ጥረት
አድርጋለች ግን የመንግስት ድጋፍ ይሄን ያህል የላትም፣
3ኛ) ኪነጥበብ አልተደገፈችም እንዳይል የተናገርኩት ተመዝግቦ ችግር እንዳይፈጠርብኝ
ኪነጥበብ ተደግፋለች እንዳይል መሬት ላይ ያለውን የሚያውቁና ህሊናው የሚታዘበው ስለመሰለው በተቀመጠበት እየታሸ ክርክሩን
የሚሰማ ነው፡፡
በሁለተኛ ረድፍ ያሉትን
የመሰጠኝን የአቶ ጌታቸው በለጠን የመከራከሪያ ነጥብ ለማሳያ እንይ እስቲ(በነገራችን ላይ በአሁኑ ጊዜ የአሰላለፍና የማሊያ
ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ከግንዛቤ አስገቡልኝ) ቀድሞ በነበረው የመንግስት ዘመን ኪነጥበብን መንግስት በየአካባቢው የመሰብሰቢያ
አዳራሽ ከመሥራት ጀምሮ የሚደረገው ድጋፍ ቀላል ነው የሚባል አልነበረም፡፡ አሁን ግን ይሄንን እምብዛም አናይም፤ ኪነጥበብና
መንግስት አልተግባቡም፡፡ ይህንን በማስረጃ ሲያሳዩ፤ የቲያትር ቤቶች የአዳራሽ ኪራይ፣ ለኪነጥበብ መከወኛ አዳራሽ አለመሰራት፣
የኪነጥበብ ማስታወቂያዎች የቴሌቪዥን ክፍያ ከፍተኛነት፣ የኪነጥበብ ስራዎች ቀረጥ ከፍተኛነት፣ የኪነጥበብ ስራዎች የአእምሮ
ውጤትና የተዛማች ጥበቃ መብት ላይ በመንግስት ተገቢ ትኩረት አለመስጠት ሌላም፤ ሌላም ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ ከሆነ
አሳቸውን ግርም ያላቸው መንግስት የኪነጥበብ ጠቀሜታ የማያውቅ ሆኖ አለመሆኑ ነው! የኪነጥበብ ጠቀሜታ የገባው የኢትዮጵያ
መንግስት ቢኖር እንደ ኢአህዴግ መንግስት ያለ የለም፡፡ በጫካ ውስጥ ቲያትር እየሰሩ፣ መዝሙር እየዘመሩ፣ ግጥም እየገጠሙ
አባሎቻቸውን እና በእነርሱ ዙሪያ ያሉትን ህብረተሰብ በመቀስቀስ ለአላማቸው መሳካት የተጠቀሙ ናቸው፤ ከአንድም ሁለት መፅሐፍ
የፃፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ነው ያለን እኮ!! የኪነጥበብ ጠቀሜታ በሚገባ ያውቋታል፤ለምን አሁን ትኩረት እንዳልሰጧት አይገባንም
እንጂ! አሉ፡፡
ይህ ስብሰባ የኢትዮጵያ ኪነጥበብ ሰዎች ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ
እንዳሉ አሰላለፉን ስናይ ምስል ከሳችነቱ አያጠራጥርም፡፡ስለ ሙዚቃ እየተነጋገርኩ ስለሆነ ወደ ሙዚቃ ልመለስ ይህ ልማታዊ
ኪነጥበብ ወይም ንቅናቄ የተባለውን ለማሳካት የተደረገው ዘመቻ አሁን እያየነው ባለው የከያኒዎች አለን አለን የሚል ሁኔታ ግቡን
እየመታ ያለ ይመስላል፡፡ ብዙ ሙዚቀኞች ከላይ ከተራ ቁጥር 1-3 የገለፅኩትን ጉዳዮች ታሳቢ አድርገው የሚለቁት ነጠላ ዜማዎች
የብሔር ብሔርሰቦችን ባህል እና ወግ በሙዚቃ በዘመናዊ ሁኔታ አቀናብሮ ሌሎች የአገሪቱ ብሔር ተወላጆች መረጃ መስጠት ሙዚቃን
ማስተዋወቅ መልካም ተግባር ነው፡፡ ችግሩ ቀደም ሲል እንደገለፅኩት የተለያየ ጥቅማ ጥቅሞችን ታሳቢ ተደርጐ የተሠሩት ሙዚቃዎች የብሔር
ብሔረሰቦችን ባህል፣ ወግና ሙዚቃ ለማስተዋወቅና ለሚዘፍኑለት ብሔር የተቆርቋሪነት ስሜት ኖሯቸው ነው ወይ? የብሔሩን ባህልናወግ
በሚገባአውቀው ሌላውን ሊያሳውቁ ነው ለማለትም አያስደፍርም፡፡ አሁን፤ አሁን በተለይ ቀደም ሲል ብዙ ባልታወቁ ብሔር ብሔረሰቦች
ዙሪያ ሙዚቃ መስራት አዋጭ የሆነ ወይም ፋሽን ነገር ይመስላል፡፡
ቀደም ሲል እንደገለፅኩት በቴሌቨዢን እና በሬድዮ ያለእነዚህ ዘፈኞች ሌላ
የዘፈን ዜማ የሌለ ይመስል ዘፈኖቹ በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙሃኖች በመቅረባቸው ምክንያት ሰው እንዲያዳምጠው ያደርጋል፣ ህፃናቶች
በጨዋታቸው መሐል አዝማቹን ይዘው እንዲዘፍኑት መንገድ ይከፍታል፣ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚዘጋጁ ብሔር ተኮር ወይም ልማት ሰበብ
ዝግጅቶች ላይ ለመጋበዝ ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል፤ አልፎ ተርፎም መሬት ሁሉ ሊያሸልም ይችላል፤ የታገሰ ጥቁር ድንጋይ ውሃ ሲመጥ
ያያል እንደሚሉት! በአሁኑ ጊዜ የሚታይ ቁጥሩ ቀላል የማይባል የኪነጥበብ ባለሙያ የሚያሳየው ካድሬ መሰል እንቅስቃሴ ልማታዊ ኪነጥበብ
አልሚ ከያኔዎችን ወደ ሸለቆው እያስባ ነው ብል የተዳፈርኩ አይመስለኝም፡፡
በማሳያ ላስረዳ፤ ቴሌቨዥን ላይ አብዮታዊ የህፃናት መዝሙሮች በዝተዋል፡፡የመዘሙሮች
መብዛት ችግር ኖሮት አይደለም የመዘሙሩ መልዕክት አይናችንን ጨፍነን ብናደምጠው ግን የአንድ ካድሬ የስብሰባላይ ስብከት አይነት
ድምጽ ነው፡፡ህፃናቶችን ምንም አስተያየት መሰንዘር አልፈልግም ከእነርሱ ጀርባ ሆነው የሚዘዉረዘቸውን እንጂ? የህፃናትና ወጣቶች
ቲያትር ቤትን ጥሩ ልማታዊ እንቅስቃሴ እየተደረገበት ያለ
ወይም እንደ ፓይለት ፕሮጀክት ለመውሰድ የሚያስችል ጥሩ ምሳሌ ይመስለኛል፡፡ እነዚህን ህፃናቶችን ግጥም ሰጥተው ዜማ ሰርተው
እጃቸውን ወደ ላይ ወደታች ፊታቸውን ፈገግ ጠቆር እያደረጉ የሚፈለገውን የካድሬዎችን ዲስኩር የሚያሰለጥነው ማን ነው ብንል ይኸው
የሙዚቃ ባለሙያ ነው፤ በተለይ ጎላ ብለው ቴሌቪዥን ስክሪን ላይ ደጋግሞ የኘሮፖጋንዳ ቋንቋና ስሜት ያዘለ መዝሙሮች ጀርባ ብቅ
የሚል አንድ የሚዚቃ ባለሙያ ወደ አእምሮአችን ብቅ ይላል፡፡(ለጊዜው
ስሙ ይቆየኝ)፡፡እነዚህ ግለሰቦች ይህ አስተዋጾአቸው የመንግስት
መንበር ሁሉ አስገኝቶላታቸዋል፡፡የህፃናቶችን የሚለሰልስ አሳዛኝ አንደበት በመጠቀም ጥቂቶችን የሚያስፈነጥዝ ብዙዎችን
የሚያስኮርፍ፣ በገሃድ የሚታይ እውነትን እንዳላየ ሆኖ የሙገሳ
አልፎም ተርፎም በቃላት ሽንቆጣ(ቆሻሻዋ……ን ጠራርጎ……….የሚለው ሀረግን ማየት ይቻላል)፡፡(የዚህ አይነት ልማታዊ ሥራ ጠቀሜታው ወንበር ብቻ
አይደለም፤ በየምክንያቱ በቴሌቪዥንና በሬድዮ እንደ የአገሬው ጀግና ቃለምልልስ የመደረግ እድልም ጭምር አለው፡፡
ሙዚቃ ስለ ልማት ቢሰብክ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች ቢያወሳ ምንም ኃጢያት
የለውም፡፡ ጉዳዩ ግን ስለብሔር ብሔረሰብ ስናነሳ ስለሚዘፍኑለት ብሔር ባህልና ወግ ያውቃሉ ወይ ብለን ስንጠይቅ ብዙዎቹ
አያውቁም ማለት ይቻላል፤ ለምሳሌ አንድ ናይት ክለብ በመጫወት ድምጹን ሲያማሽ የነበረ አንድ
ጀማሪ ሙዚቀኛ ቴሌቪዥኑን ሞልቶት አይተናል፤ለምን የዚህ ሰው ምስል ተደጋገመ ቢባል የብሔሮች መገኛ ምናምን ምናምን በማለት
"አገሬ" ብሎ ግጥሙን ስላሰረው፡፡ ይህ ሰው ስለ ብሔር ብሔረሰብ ያነሳው
የመጀመሪያዉ መስመር ላይ ባሉት የግጥም አንጓዎች ላይ ነው፡፡ (በእርግጥ የተለያ የአገራችን ብሄር በሄረሰቦች ባህላዊ ዜማን አካቷል)
ይህ ዜማ አርቲስቱን ናይት ክለቦችን እያማረጠ እንዲሰራ ሳያረገው አልቀረም ባይ ነኝ፤ የሚገርመው ይህች
"አገሬ" እያለ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ሙዚቃ ቀላቅሎ በብፌ መልክ የሰራውን
ሙዚቃ አዋጭነቱን
አይቶ ይህን መሰል ዜማ ደግሞ በለብ ለብ አድርሶ በቴሌቨዥንበድጋሚ አሳይቶናል፣ እንደ
ቀደሞው ግን ብዙ የተሳካለት አይመስለኝም፣ ይህ ዘፋኝ በብሔር ብሔረሰቦች ስም ለሚዘፍንለት ብሔር
ግራ የሚያጋባ የራሱን ቃላት እያነበነበ ወይም ትርጉም የሌለው ድምፅ እያሰሙ በመጫወት
በስሌት የሚንቀሳቀሱ
አርቲስቶችን ለመግለፅ የተሻለ ማስረጃ ይሆናል፤ ይህ ሰው በዚሁ
አገሬ በሚል በሚጫወተው ዜማው የወላይታ ሙዚቃ እንዲወክል አድርጐ የተጫወተው ዘፈን ዜማው የወላይታ ሆኖ ቋንቋው ግን የራሱ ነው፡፡
ወላይተኛ ለማያውቅ ሰው ትንሽ ሊያደናግር ይችላል እንጂ ቋንቋውን ለሚያውቅ ሰው ግን በሰው ቋንቋ ያፌዘ ያህል ነው
የሚወሰድለት፤ ምክንያቱም ትርጉም የሌለው የራሱን ወላይተኛ ስለሚያወራ!! ይህን ብቻ አይደለም ትርጉም የሌለውም ቢሆን አንደ
ቃል ብቻ በመደጋገም ናይት ክለብ ያለ ይመስል በቴሌቭዥን ሲከትፍ አይተናል
እነዚህንና ሌሎች በተለያየ የመንግስት የሰበብ እና ከጀርባቸው ድብቅ ዓላማ የያዙ በብሔር ብሔረሰብና በልማት ስም የሚሰሩ
ዝግጅቶች ላይ አይናቸውን እያፈጠጡ የኘሮፖጋንዳ ማጀቢያ ስራ የሚሰሩ ታዋቂ አርቲስቶችም እያየን መምጣት ጀምረናል፡፡
ይህንን
ፅሁፍ የሚያነብ ሰው ስለ ብሔር ብሔረሰብ መዝፈን ስለ ልማት መዝፈን ምንድን ነው ችግሩ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፤ የኔ መልስ ምንም
ነው፣ ችግሩ ግን ስለብሔር ብሔረሰብ ሲዘፈን የብሔር ብሔረሰቡን ወግን ባህልን ማእከል አድርጐ ነው ወይ ነው ጥያቄው! ዓላማው
መንግስት የተለየነጥብ (score)፤ አስመዝግቤያለሁ በሚለው የብሔር ብሔረሰብ የእኩልነት የታይታ ጨዋታ ማዳመቂያ ስራ
መስራታቸው እንጂ!! ልማት፤ልማት እያሉ ልማታዊ ሙዚቃ እንሰራለን ሲሉ የትኛው ልማት ምን አይነት ልማትን ነው እያልን ያለነው፡፡
አሁን አሁን ልማታዊ ነጋዴ፣ ልማታዊ ኢንቨስተር፣ ልማታዊ እንቅስቃሴ ማለት መሬት ላይ ወድቆ ስናይ ገዢው መንግስት እየከወነ
ያለውን ለራሱ የስልጣን እድሜ ማራዘሚያ የሚጠቅሙ በአብዛኛው ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍልን የሚያጎሳቅልና ለስቃይ የሚዳርግ
ሊባሉ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች የሚደግፉ፣ ከመንግስት ሙሰኛ ባለስልጣናት ጋር በሽርክነት
በጋራ የሚሰሩ ባለሀብቶችን ወይም ነገ በሆነ ምክንያት ያጠቁኛል
በሚል በፍርሃት ቆፈን የሚንቀሳቀሱትን ግራ የገባቸው ባለሃብቶችን ማለት
ያህል ነው የሚል ትርጉም የማይሰጥ ስለመሆኑ ዋስትና መግባት ያስቸግራል፡፡
ለአገር የሚጠቅሙ የህብረተሰቡን መልካም እሴት፣ አንድነት፣ኢኮነሚያዊ
ጠቀሜታ፣ የተሻለ በመተሳሰብና በመከባበር የሚኖር መልካም ትውልድን የመፈጠር ጉዳይን አትኩሮ
የሚሰራ ስራዎች ወይም ሰሪዎች የአህያዋን አይነት እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ነው እንቅስቃሴው፡፡ ታዲያ ይህንን እያጀቡ እያዜሙ ነው ልማታዊ ሙዚቃ ሰርተዋል፣ ሰርተናል የሚሉት እንጂ
ስለ እውነተኛ ልማት መስራት መች ኃጢያት አለውና፤ ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ መግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ሙዚቀኛው በሙዚቃው
ህብረተሰቡን ታሳቢ ያደረገ ስራ መስራት አለበት ነው እሳቤዬ፡፡ እኛ አገር ውስጥ ህዝቡን የሚያስጨንቀው ብዙ ማህበራዊ
ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች አሉ ለዚህ እህህ!. . . ለሚል ህዝብ ማን ብሶቱን ቢያንስ በሙዚቃ ይተንፍስለት?! በነገራችን
ላይ የህዝቡን ስሜት ብሶትና ቁጭት ማእከል ያደረጉ ግጥሞች ያዘሉ
ሙዚቃዎችን መጫወት አደገኛ ነው ቢባል እንኳን አሁን አሁን ብቅ ብቅ ብለው የሚታዩትን የሀዘን ስሜትና የሙሾ ወረዳ አይነት
ያላቸው ዜማዎች ምንያህል የህብረተሰቡን ቀልብ የሳቡና አዋጭ መሆናቸው ህብረተሰቡ ውስጥ ያለ ሰው በቀላሉ የሚያረጋግጠው ነው፡፡
ሙዚቃ መንገድ ትመራለች እያልን እንዳልነው የሆድ መስመር ውስጥ ያሉ
ህሊና የሌላቸውንም ለመገሰፅ ከእኩይ ተግባራቸው እንዲመለሱ መካሪ ሆኖ ሁሉ ህብረተሰቡን ልታገለግል ትችላለች፤ ይህንን ተግባር
ከልባቸው በእሳት ውስጥ እየተራመዱ የሚከወኑ የሉም ለሚለው ድንገተኛ ጥያቄ ጥቂት ሆኑ እንጂ!አሉ!! በሚቀጥለው ጹህፌ በሁለተኛ
ደረጃ ስላስቀመጥካቸው መንበር ናፋቂ ተዋንያን እዳስሳለው፡፡ በዝራው
አሻግሬ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ