ረቡዕ 1 ኤፕሪል 2015

ይድረስ ለባዶ ራሶች!



ይድረስ ለባዶ ራሶች!
  
   ይህ መልዕክት በተለያየ ቦታ ሆነው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ለሚያደክሙ፣ ለሚያሳምሙ፣ለሚያራቁቱ፣ለሚያሰቃዩ በህሊናው ኢትዮጵያኖች ስም የተጻፈ የኢትዮጵያ ራዕይ ነው፡፡
           በተለያየ ወንበር ላይ ተቀምጣችሁ እናንተና እናንተን ብቻ የምታዩ፣ ያለእናንተ አዋቂ የሌለ የሚመስላችሁ ማሃይሞች በገረወይና ጭንቅላታችሁ ስትነኩ ከመጮህ በስተቀር ማስተዋል የሌላችሁ፡፡ ምላሳችሁ የሚርገበግብ አንገታችሁን ዞር አድርጋችሁ ለማየት የተሳናችሁ በገዛ እጃችሁ አንገታችሁን የቀሰራችሁ፡፡ ቢሮአችሁ ውስጥ ኢትጵያዊነትን ለማጥፋት ተግታችሁ የምትሰሩ፡፡ ወንደማችውን ጠላት ጠላታችሁን ወዳጅ የምታድርጉ፡፡ አይናችሁ የፈጠጠ ግን የማያይ፡፡ ጆራችሁ የቆመ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የሲቃ ጨኹትና እሪታ የማይሰማችሁ፣ ታሪክ የምትከልሱ የምታፈርሱ  የራሳችሁን የተሳሳተ ታሪክ በጉልበት የምታስውጡ፡፡ ድንቁራናችሁ ያልገባችሁ ቀሽም ድራማ ፈትቶ ለሚገጥማችሁ ህዝብ የምትሰሩ፡፡ አይኔን ግንባር ያርገው የደንቆሮ ለቅሶ የማይገባችሁ፡፡ ህሊናችሁን ፈጥፍጣች በእግራችሁ የጨፈለቃችሁ፡፡ ንጹህነት ጠላታችሁ፡፡ መልካም መሥራት ሴጣናችሁ፡፡ ህግ ማክበር እብደታችሁ፡፡ በቴሌቪዥን በሬድዮ፣በአዳራሽ በሆቴሉ የውሸት የምትለፍፉ፣ ዶሮ ሳይጮህ ጩህታችሁ መቶ ጊዜ ውሃ የሚበላው የጮሆኃችሁበትን ሰነድ በእግራችሁ የምትረጋግጡ፡፡ የራሳችሁን ጩህት ለራሳችሁ የምታዳምጡ፡፡ ህይወት ጤፉ፣ አዛውንት፣ ሽማግሌ፣ የሃይማኖት መሪ፣ እርጉዝ፣ እመጫት፣ ሴት፣ ህጻን፣አቅመ-ደካማ የማይገባችሁ፡፡ የኢትዮጵያዊያን ደም ጥቁር ነው የምትሉ፡፡ እናንተ ወራሪዎች ኢትዮጵያን የማፈራረስ ስራ የምትዳክሩ፡፡
          አናንተኛዎቹ ደግሞ! ከኃላ ከኃላ ጡልጡል እያላችሁ ንጹህ የምታስፈጁ፣ በመኪና መንሸራሸራችሁ፣ ህንጻ መገንባታችሁ ብርቃችሁ፡፡ የስምዝርዝር እየሰጣችሁ በድንጋይ የምታስወግሩ፣በጥይት የምታስደበድቡ፣ የእኛ ነው የእነሱ ነው እያላችሁ እንደ ቅርጫ በመመደብ ሰው በቁም የምትገሉ፡፡ ወንድም እህታችሁን እናት አባታችሁን ለሆዳችሁ ለክርሳችሁ ብላቻሁ የምታስፈጁ፡፡ ኢትዮጵያዊ ስነልቦና ከውስጣችሁ ያጸዳችሁ፡፡ በሰው ህይወትና፣ ኑሩ ቁርጥ የምትቆርጡ ወስኪ የምትለጉ፡፡ አንድ ኪሎ ሥጋ ለመግዛት የትየለሌ ሰልፍ ጸሃይ አናቱን እየወቀረው በሚጠብቅ የአገር እድገት ላም አለኝ በሰማይ የሆነበት ህዝብ ላይ ሙድ የምትይዙ፡፡ ነገ ማለት የማታስቡ፣ ልጆቼ፣ሀገር ፣ትውልድ መጥፋት ለቅንጣት ያህል ስሜት የማይሰጣችሁ፡፡ የተለያያ ካባ ለብሳችሁ ያለቆቻችሁን  መፈክር ጉሮሮአችሁ አስኪነቃ ድረስ የምታስተጋቡ፡፡ ጎረቤት፣ቤተሰብ፣ዘመድ ሰው ምን ይለኛል የማትሉ፡፡ አንገታችሁ ላይ የተቀመጠውን ገረወይናችሁን ነቅነቅ ማድረግ እንኳን ያልቻላችሁ፡፡ እከሌ እንደዚህ ነው… እከሌ ደግሞ….. እንደዚህ እያላችሁ ደምወዝ የሚከፈላችሁ፣ቤት የሚሰጣችሁ፣ መኪና የሚለገሳችሁ፣ መሬት የምትወሩ፣ይምታስወርሩ፣የደሃ ቤት የምታስፈርሱ ለሃብታም ደሃ የምትጠርጉ፣ጎዳና ተዳዳሪ በየእለቱ የምትፈለፍሉ፣ በአንድ ብርሌ ቤት የምትንዱ፣የምታስንዱ፡፡ ከራስ በላይ ህግ የምትሉ፡፡ ድንጋይ ትራስ አድርጎ አውላላ ሜዳ ላይ የሚተኛን ህዝብ በስፖንጅ ፋራሻችሁ መተኛት አቅቷችሁ በድንጋይ ትራስ የምተቀኑ፡፡ ንኮች!   
   እናንተ የእውር መሪዎች፡፡ በማይረባ ጥቅማጥቅም በህዝብ ስሜትና ህይወት ጥባጥቤ የምትጫወቱ፡፡ ኑሮአችሁን ለማደላደል ሳይጠራችሁ አቤት፤ ሳይልኩአችሁ ወዴት የምትሉ፡፡ በነጻ ሞያተኛ ስም ሸፍጥ የምትሰሩ፣ ከርሳችሁን የምትሞሉ፡፡ ባገኛችሁት መንበር ምላሳችሁን  የምታንቀጠቅጡ፡፡ የራበው ህዝብ መሪዎቹን እንደሚበላ እናንተ የገዳዮች አሽከሮችን መብላት ብቻ አይደለም በጥርሱ ያኝካችኃል! ይሰለቅጣችሁልም! የተቀበላችሁት እጅ መንሻ፣ በግፍ የከመራችሁት ሀብት የተራራ ያህል ቢቆለልም መደበቂያ አይሆናችሁምና፡፡ ሚለየን ብራችሁ አይናችሁ እያየ ጉም ይሆናል፡፡ በፈጠራ ወሬያችሁ የናዳችሁት ታሪክ፣ ያፈረሳችሁት ቤት፣ማህበር፣ ህዝብ የመጨረሻው ሰዓት ላይ ፊታችሁ ለፍርድ ይቀርብላችሁና ሴጣን አሳስቶኝ ነው፣ለእንጀራዬ ነው፣ መሳሪያ ተደቅኖብኝ ነው፣አማራጭ ስሌለኝ ነው፣አህምሮዬ ተሰውሮብኝ ነው፣መድሃኒት ተደርጎብኝ ነው ብላችሁ ብትመልሱ አጠገባችሁ ሲጮህባችሁ ጆራችሁን ይዛችሁ አልሰማሁም የማሪያምን ብቅል እፈጫላሁ እያላችሁ መደንቆራችሁ አይጠቅማችሁምና ያን ግዜ ወየውላችሁ፡፡    
  ለወጋናቸው አለው የሚሉ ንጹህ ኢትዮጵያውያኖችን እንደ እብድ የመትቆጥሩ፣ ቀውሶች! ባልደረቦቻችሁ ለህሊናቸው ሲኖሩ እናንተ ሆዳችሁን ማሳበጣችሁን እንደ ውጤታማነት እየጠቀሳችሁ ስም የምታጠፉ፣ ለማሰጠፋት ቀድማችሁ እጃችሁን የምትቀስሩ፡፡ ጨለማ ውስጥ  ሆናችሁ የጸዳ ሰው ለማጥፋት የምትረባረቡ፡፡ ፍርፋሪ ለመልቀም ሬሳ የምታስነሱ፡፡ እስርቤት ባሰገባችሁቸው እህትና ወንድማቾቻችሁ ስቃይ እናንተ የምትዝናኑ፣ ቂጣችሁን የምታሰፉ፣ በየሆቴሉ የአንድ ፍሬ ህጻናትን ገላን የምታረክሱ፡፡ ሲያሻችሁ በኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘብ መሬት አይንካኝ ብላችሁ የድሃ ልጅ፣ የታጋይ ልጆች አፈር ሲበሉ፣ የእናት የአባት ያለህ ሲሉ እናንተና በአጢያት የፈለፈላችሃቸው ምንዓልባት ነገ እናንተ ብታመልጡ እንኳን እነሱ ፍዳቸውን የሚቆጥሩበትን የክፋት የማዕዘን ድንጋይ ያኖራችሁ፡፡   
እውነት እውነት እላችኃለው! ይህን ህዝብ ያጤሳችሁትን ያህል በሰፈራችሁት ቁና ተመርቆ ተዝቆ ይከፈላችሁል፡፡ ሰማዩ ጠቁሮ ሲታይ አይናችሁ አላይም ያላችሁ ምልክት ይሁናችሁ! የእናንተ ክፍት የመጨረሻ  ሰዓት ላይ መድረሱ ነው፡፡ እውነት እውነት እላችሃለው ይህ አይኑ ደም ለብሶ የሚያያቸሁ ሀዝብ በሶ ጨብጦ፣ደንጋይ ፈልጦ የእናተን ቡራኬ አይጠብቅምና ያን ጊዜ ወየውላችሁ! ማህበራችሁ፣ጉርሻችሁ፣ነፍጣችሁ፣ቁርኝታችሁ፣የተደገፋችሁት የሀሰት ግንባችሁ እንደ ጉም ብን ብሎ የሚቀር ነውና ያን ግዜ ወየውላችሁ! የእናታችሁ ቀሚስ፣  የሚስታችሁ ቀሚስ በህጻናት አምላክ ብላችሁ የህጻን ሴት ልጆቻችሁም ቀሚስ መደበቂያ አይሆናችሁምና፡፡
  እውነት እውነት እላችኋሃለው በቤቲክርስቲያን ውስጥ እንደ ካህን በመስጂድ ውስጥ እንደ ሼክ ለብሰው አመራር የሚሰጡ የሚቀበሉ አብዮተኞኝ ሲበዙ ያን ጊዜ አብዮት ራሷን ልተባላ ነውና ወደ ውስጥ ተመልከቱ!
አውነት እውነት እላችኋለው ለሀገሬ እያሉ ለጌታቸው እያቅራሩ፣እየጨፈሩ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ ሀገርና ጌታቸውን መለየት አልቻሉምና ወይም በሀገሬ ሰበብ ሆዳቸውን እየሞሉ ነውና ይህን ጊዜ አለን አለን ከሚሉ የቀለም ሽፍታዎች ጨኽት ምድብ ያልተለዩ ስለሆነ ያን ጊዜ በእውነት ላይ ሴራ እየተሰራ ስለሆነ ምልክቶችን ከወደ ምስራቅ ተመልከት፡፡  
   እውነት እውነት እላችኋለው! ጭፈራ ሲበዛ፣ ግርግር ሲመጣ፣ የራበው ህዝብ አንጀቱን ጨምቆ ራበኝ ማለት ሲያቆም፣ በእናንት  ግፍ ፍትህ አጥቶ እሲክርበው ሲጨሁ የነበረ ህዝብ ድምጹን ሲያጠፋ ያን ጊዜ ጊዜው ደርሳልና ወየውላችሁ፡፡ ነብሮች ድመት ድመቶች ነበር ሲሆኑ፣ የተማረ ያስተምር ያልተማረ ይማር የሚለው ተገልብጦ ያልተማረ ያስተምር የተማር ይማር የሚል መፈክር የበዛ ጊዜ የምትረግጡት መሬት ሊሰምጥ ነውና ያን ግዜ ወየውላችሁ፡፡
    ሀገሬ የሚሉ፣ አሁንስ በዛ፣ፍርዓት እራሱ ይፍራን፣ ሰይፍ አንፈራም ከሰይፍ የበለጠ እኛ ስል ነን የሚሉ ሰዎች ብቅብቅ ማለት ሲጀምሩ ያን ጊዜ ምልክት አይታችሃልና የእናቴ መቀነት ጠለፈኝ ሳትሉ ከንፋስ በፈጠነ ሁኔታ የማስመስል ለፍርፋሪ ለቴሌቪዥን ሳይሆን ለህዝብ የእውነት ሀገሬ ከሚሉ ወገኖች ተርታ ሳትሰለፉ የቀራችሁ ዕለት በግራ የመቆማችሁ ምልከት ይሁናችሁ፡፡                              
  ከአህያ ቆዳ የተሠራ ቤት፣ ፍርስርስ ይላል ጅብ የመጣ ዕለት፤ የሚባለውን ተረት የሚተርት ሲበዛ ቀኑ የተቃረበ ጊዜው የደረሰ መሆኑን በራዕይ አይነገርምና ያን ጊዜ ወየውላችሁ!!
    በዝራው አሻግሬ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ