አርቲስት በህዝብ መዳፍ ላይ እንዳለ እንቁላል ነው!
አርቲስት ማለት ተዋናይ፣ዘፋኝ፣ሙዚቀኛ፣ ኮመዲያን፣ዳንሰኛ፣ሠዓሊ፣ ቀራጺ ወዘተ.. ሊባል
ይችላል ብንል የተለያዩ ጹህፎች (literatures) ላይ በተለያየ
አገላለጽ መጠቀሳቸው ዋቢ ማድረግ ይችላል፡፡ ይሁንና አርቲሰት
የሚለው ቃል የእንግሊዘኛው ARTIST ከሚለው ቃል የተወሰደ ስለመሆኑ
ግልጽ ነው፡፡ አርቲስት የአማርኛ አቻ ትርጉም ጠፍቶት ነው የእንግሊዘኛውን
Artist የሚል ቃል የወረስነው ጥበብ፣ ጥበበኛ፣ የኪነጥበብ ሰው ልንል አንችልም ይሆን?! አሁን በህብረተሰቡ ውስጥ ሆነ በተለያየ
የመገናኛ ብዙሃን አርቲሰት እከሌ፣ አርቲስት እከሊት በማለት የእንግሊዘኛውን ቃል ለአበሻ የኪነጥበብ ሰዎች እንደማዕረግ ተሰጥቶአቸው እንሰማለን፣አናነባለን እንመለከታለንም፡፡
የአንግሊዘኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት Art የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል ጥበብ፣ ብልሃት፣ ዘዴ በማለት ሲገልጸው
artist የሚለውን ቃል ደግሞ
ሰዓሊ፣ የኪነጥበብ ሰው በሚል ትርጉም ይሠጠዋል፡፡ የኢትየጵያ ቃንቃዎችና
ጥናትምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም ባዘጋጀው መካከለኛ ዘመናዊ መዝገበ
ቃላት በሚል የሚመደበው መዝገበቃላት ላይ «ጥበብ» ለሚለው ቃል ብልሃት፣
ዕውቀት፣ ዘዴ በሚል ፍቺ ስጥቶ የዚህ ቃል የሥም ገላጭ ቃል የሆነውን «ጥበበኛ» የሚል ቃል አዋቂ፣ ብልሃተኛ፣ ዘዴ የሚያውቅ በማለት
ይፈተዋል፡፡
አርቲስት/Artist፤
አርት/art ከሚለው የእንግሊዘኛ ቃል የተወሰደ መሆኑን የተለያየ የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላቶች ያሳያሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የህግ
ቃላቶችን ወይም ሀረጎችን በመተርጎም ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው ብላክ ሎው (Black law) የህግ መዝገበ ቃላት እና በርካታ ሰው በማመሳከሪያ የሚጠቀመው ዊኪፒዲያ ኢንሳይክሎፒዲያ መዝገበ
ቃላትን የጥበብ/አርት(Art) እና ጥበበኛ/አርቲሰት(Artist) ትርጉምን
እንዴት እንደሚገልጹት እንይ፡-
1. Black law Dictionary፡-
Art
1. The
methodical application of knowledge or skill in creating something. .
2. An
occupation or business that requires skill; a craft.
3. Patents. A process or method that
produces a beneficial physical effect.
በሆነ ነገር በመፍጠር ሂደት ላይ ዕውቀትንና ችሎታን ማስፈጸሚያ ዘዴ፣ ችሎታ የሚጠይቅ የሞያ ወይም የንግድ
አይነት/ የእጅ ሞያ፣ የፈጠራ ባለቤትነት መብት፤ ጠቃሚነት ያለው
ግዙፍ ውጤት የሚሰጥ ሂደት ወይም ዘዴ፤
2. Wikipedia,
the free encyclopedia
Art is a diverse range
of
human activities
and the products of those activities. In their most general form these
activities include the production of works of art, the criticism of art, the
study of the history of art, and the aesthetic dissemination of art.
ዊኪፒዲያ ፍሪ ኢኒሳይክሎፒዲያ መዝገበ ቃላት፡-
ጥበብ ማለት
መጠነ ሠፊ የሆነ የተለያዩ የሰው ልጅ ተግባርና የተግባሩ ውጤት፡፡
በአጠቃላይ መልኩ ሲገለጽ ይህ ተግባር የተግባሩን የሥራ ውጤት፣
ተግባሩን መተቸት፣ የተግባሩን የኃላ ታሪክ ማጥናት እና
ተግባሩን በማራኪ ሁኔታ ማሰራጨትን ያካትታል፡፡
ጥበበኛ/አርቲሰት/Artist የሚለውን ቃል ደግሞ ዊኪፒዲያ ፍሪ ኢኒሳይክሎፒዲያ
መዝገበ ቃላት እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡
An artist is a person engaged
in one or more of any of a broad spectrum of activities related to creating art, practicing the arts, and/or demonstrating an art. The common usage in both
everyday speech and academic discourse is a practitioner in the visual
arts only. The term is often used in the
entertainment
business, especially in a business context, for musicians and other performers
(less often for actors).
ጥበብን መፍጠር ፣ተግባራዊ
ከማድረግ እና ሠርቶ ከማሳየት ጋር በተያዘ ከአንድ በላይ በሆኑ በእነዚህ
ሰፊ ህበረቀለም ባላቸው ተግባሮች የተሰማራ፡፡ ይህ ቃል በዕለት ዕለት
ንግግራችንና ትምህርታዊ ገለጻዎች ላይ ለሥነ ጥበብ ባለሞያ ብቻ እንደሚያገለግል ተደርጎ በተለምዶ ይወሰዳል፡፡ ቃሉ ዘውትር ጥቅም ላይ የሚውለው ለመዝናኛ ሥራዎች፣ በተለይ ለሙዚቀኞችና ሌለሎች ከዋኞች
ነው( እምብዛም ለተዋናዮች መጠሪያነት አያገለግልም)፡፡
አርት(Art)እና አርቲስትን(Artist)መደበኛ የማይክሮ
ሶፍት(Microsoft Word) እና ዊኪሸነሪ(wiktionary)
መዝገበ ቃላት ቀለል ባለ ሁኔታና በተለመደ መልኩ እንዲህ
ይገልፁታል፡፡
Microsoft Word
Art:
- talent, ability, drawing, skill, fine art, painting, sculpture, knack etc. /ተስጥኦ፣ችሎታ፣
ሥዕል፣ ዕውቀት ፣ሥነጥበብ፣ ቅብ፣ቅረጻ ቅርጽ ፣ቅልጥፍና ወዘተ…..
Artist:
- performer, dancer, musician, Actor, comedian, singer etc… /ከዋኝ፣ ዳንሰኛ፣ ሙዚቀኛ፣ ተዋናይ፣
ዘፋኝ ወዘተ….
Wiktionary
- A person who creates art.
- A person who creates art as an occupation.
- A person who is skilled at some activity.
ጥበብን
የፈጠረ ሰው፣ ጥበብን በመጠበብ ሥራው ያደረገ፣ በሆነ ተግባር ላይ ባለዕውቀት የሆነ፡፡ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡
መነሻው በመጠኑ
ይህ ከሆነ በሌላ መልኩ ደግሙ በእርግጥ አንድ ሰው አርቲሰት ነው
ልንለው የምንችለው ምን አይነት የአርት ወይም የጥበብ ሥራ ሲሰራ
ነው?! አንድ ድራማ ወይም አንድ ዜማ የተጫወተ ሰው አርቲስት ነው ሊባል ይችል ይሆን?! የሠራው ሥራ ጥራቱ፣ ጥልቀቱ፣ ማህበራዊ
ኢኮነሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታው ወይ ፋይዳው፣ እርካሽነቱ፣ ድሪቶ
መሆኑ፣ የተሰረቀ ወይም የተገለበጠ(plagiarism) መሆኑ፣አዝናኝነቱ፣ ቢዚነስ ተኮርነቱ፣አሸር በአሸርነቱ፣አሸርጋጅነቱ፣ የፕሮፓጋዳ
መንፈስ ያለው መሆኑ፣ በልታይ ባይነት የተሰራ መሆኑ አርቲስት የሚለውን ሥም አይገባውም፤ ይገባዋል የሚለውን የሚመልስ ነውን?!
የሚለው ጥያቄ ብዙ ሊያነጋር የሚችልና ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡
አሁን
ባለው ሁኔታ አርቲስትነት ከላይ ከገለጽናቸው ተግባሮች አንዷን የሰራ እኔ አርቲስት ነኝ በሚለው ወይም የእንግሊዘኛው Arty የሚለው
የአንግሊዘኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት የሥነ ጥበብ ሰው ነኝ ባይ በሚል
የሚተረጉመው አይነት እና የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃኖች በእነርሱ በጎ ፍቃድ አርቲስት እከሌ በሚል የጠሩት ወይም ህዝቡ በራሱ መንገድ
አርቲሰት ብሎ በሰጠው ስያሜ ነው አርቲስትነት፡፡
የአገራችን የቅጅና ተዛማች መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/96 አንድ ሰው በአህምሮ ያሰበውን በወረቀት ወይም ግዙፍ በሆነ ነገር ላይ በማሳረፍ
ከምናብነት ወደ ግዙፍነት ሲቀይረው የፈጠራ መብት ጥበቃ አንደሚደረግለት
በአንቀጽ 6 ላይ ተገልጿል፡፡ ይህ ማለት እንግዲህ አንድ
ህጻን ልጅ በወረቀት ላይ በደመነፍስ የጫጫረውን ምስል የሚመስል ነገር
ቢሆንም አዋጁ የቅጂ መብት ጥበቃ አለው ወይም ማንም ሰው ሊቀዳበት አይችልም እንደማለት ይወሰዳል፡፡ ምናልባት የሆነ
ሥነ-ጥበባዊ ጉዳይ የፈጠረን ግለሰብ አርቲስት የምንል ከሆነ በህጉ
መሰረት ትርኪምረኪ ቢሆንም ግለሰቡ ራሱ የሠራው ወጥ ሥራ ከሆነ ፈጣሪ ነው ወይም አርቲስት ነው ልንል የሚያስችለን አንድ የአርቲስት
ትርጉም ከዚህ አንቀጽ ላይ ልንመዝ እንችላለን፡፡
በተመሳሳይ እዚህው አዋጅ ላይ በአንቀጽ 19 ከዋኝ የሚለውን ቃል አንዲህ
በማለት ይገልጸዋል፡፡
ተዋናይ፣ ዘፋኝ፣ ዘማሪ፣ሙዚቀኛ፣ ተወዛዋዥ እና ሌላ ማንኛቸውንም የሚተውን፣
የሚያወጣ፣የሚጫወት፣የሚዘፍን የሚያዝናና ወይም በሌላ ማንኛቸውም አኳኋን የስነ ጹህፍና የኪነጥበብ ሥራ የሚከውን ግለሰብ ነው፤ ይለዋል፡፡
ይህ
ትርጉም ምንአልባት ከዋኝ ከሚለው ጋር አርቲስት የሚለውን አዛምደን ብንወስድ
በዚህ ጹህፍ በግቢያ ላይ ስለአርቲስት ዝርዝር ትርጉም ከተሰጠው ጋር የሚመሳሰልና በተለምዶ ከምንጠቀምበት ማዕረግ ጋር በሚቀራረብ መልኩ የተሰጠ የህግ ትርጉም ነው፡፡
ዊኪሊ ፒዲያ ፍሪ ኢንሳክሊፒዲያ አርቲስት የሚለውን ቃል ሲተረጉም ደግሞ፡-
“an artist is a person engaged
in one or more of any of a broad spectrum of activities related to creating art, practicing the arts, and/or demonstrating an art.”
ጥበብን መፍጠር ፣ተግባራዊ ከማድረግ እና ሠርቶ ከማሳየት ጋር በተያዘ
ከአንድ በላይ በሆኑ በእነዚህ ሰፊ ህበረቀለም ባላቸው ተግባሮች የተሰማራ
በማለት ከአንድ በላይ የአርት ሥራ ላይ መሳተፍ አርቲስት የሚለውን
ማዕረግ ለማግኘት መሟላት እንዳለበት ያሳያል፡፡ (የእንግሊዘኛ ጹህፎች አማርኛ ትርጉም የፀሐፊው ነው)
ለማንኛውም በዚህ የማዕረግ ስም አጠራር ላይ ተገቢው ጥናት ተሰርቶ መግባቢያ የማዕረግ
ቃል ላይ እስኪደረስ እኔም ለጊዜው ለዚህ ጹህፍ ዓላማ እንዲረዳኝ አርቲሰት እያልኩ ጹህፌን እቀጥላለቀው፡፡
ለመግቢያ ያህል ስለ አርቲስት ማን ነው? ምን ማለት ነው? የሚለውን ሀሳብ
መነሻ ነገር ካስያዝኩ ወደ ተነሳሁበት
በቅርብ ጊዜ በሬድዮው በቴሌቪዥኑና በተለያየ መድረክ ያዙኝ
ልቀቁኝ ስለሚሉት ሠራዊት መራሽ አርቲስቶች አንድ ዘገባን መሰረት ያደረገ ትዝብቴን ወደ ማሰነበቡ ልግባ፡፡
ከዚህ ቀደም በአንድ ሁለት መጽሔት ላይ መንበር ናፋቂ ከያኒዎች በሚል ርዕስ በአቋራጭ መበልጸጊያና መንበር ፍለጋን አልመው የሚሯሯጡ አካሄዳቸውን
ምድብ፣ ምድብ በመስጠት ለአንባቢ ግንዛቤ ለመስጠት ሞክሬአለው ፡፡
በአሁኑ ሰዓት የተወሰነ የአሰላለፍ ለውጥ እየአየን ቢሆንም ከህዝብ ማዶ ካለው ሰልፍ በሚገርም ሁኔታ በመመንጠቅ የህዝብ ጉያ ውስጥ የገቡ፣ ሳይነካኩ እስከ መክሊታቸው በጨዋነት፣ በክበር ያሉ፣ ከህዝብ ጎን መቆም ወይም ሞት ያሉ ታዋቂ አርቲስቶች አሉ፡፡ በአንፃሩ በኪነጥበብ
ሞያ ውስጥ ረጅም ዕድሜ አስቆጥረዋል የሚባሉ ምደባቸውን ወደ ማዶ
ያደረጉ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አርቲስቶችም ድምጽ ማጉያ ይዘው
መፈከር ሲያሰሙ አስተውለናል፡፡ አንድ አርቲሰት በአንድ ወቅት የመንግስት ኃላፊዎቸ ጽፌ ያዘጋጀውትን ቲያትር የተለያየ ትርጉም ሰጥተው
ለህዝብ እንዳይቀርብ አደረጉብኝ በማለት ብሶት ሲያሰማ የነበር በአሁን ወቅት አሰላለፉን በመቀየር በኪነጥበብ ስም
ወደ ሀብት ጉዞ ሰራዊት መር ተርታ መቀላቀሉ አይተናል፡፡ በቴሌቪዝን፣ በተለያዩ ምክንያት በሚዘጋጁ ዝግጅቶች ላይም እምቢ!
እምቢ ላገሬ! ሲልም ታዝበናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ሠራዊት መር አርቲሰቶች አይናቸውን አፍጥጠው ያዙኝ ልቀቁኝ ማለታቸው የአደባባይ
ሚስጥር ነው፡፡ ስለመንበር ናፋቂ አርቲስቶች ስናነሳ አርቲሰት ሠራዊት ፍቅሬ በአርቲሰት ማዕረግ ነጋዴ ከሆኑትና
በተገኘው መድረኮች የአገሪቱ እጣ ፈንታ በእጃቸው ከነበረው ከሟች
ጠቅላይ ሚንስትር አጠገብ ጎን ለጎን መቀመጥን ጨምሮ በተለያዩ መንግስት
ሰራሽ መድረኮች ላይ ፊጢጥ ከሚሉት የጊዜው አርቲስት ነጋዴዎች ዋኖቹ ተርታ ልናነሳው የምንችለው ግለሰብ ነው፡፡ ምናልባትም አሁን እዩኝ እዩኝ ሲሉ የምናያቸው አርቲስቶች የሠራዊት ፍቅሬን በአርቲስትነት መነሻና ከገዢው መንግሰት ጎን የመቆሙ ምክንያት የአርቲሰቱ
ባለሀብትነትን ታሳቢ በማድረግ ወደ ልማታዊ ባለሀብትነት ጎራ መቀላቀልን
የዕቅዳቸው ግብ በማድረግ የሚራወጡ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ወደ ዘገባው
ልግባ፡፡
በ19/4/2007 ዓ.ም የወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ የፊት ለፊት ገጽ ላይ «ኢሕአዴግ የታጋዮችን ዓላማ በሚያረክሱ ሹማምንቶቹ ላይ ዕርምጃ
እንዲወስድ ጥያቄ ቀረበለት» የሚል
የዜና ዘገባ አይቼ ውስጡን ገልጬ ሳይ እነኚህ
የህወሓት የተመሰረተበትን 40ኛ ዓመት ሊያከብሩ የሄዱት ባለ ራዕይ አርቲስቶች ያቀረቡት ጥያቄ መሆኑን ስረዳ ፈገግ አሰኘኝ፡፡ ምን ማለት ነው ብዬ ራሴን
መልሼ ጠየኩት፡፡ የዜናው የመጀመሪያ አንቀጽ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
#የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ
(ሕወሓት) 40ኛ የልደት ዓመት አስመልክቶ፣ ድርጅቱ የተመሠረተበትን በረሃና በትጥቅ ትግሉ ወቅት እንደ ጽሕፈት ቤት ሆነው ሲያገለግሉ
የነበሩት ታሪካዊ ዋሻዎች፣ እንዲሁም የደርግ 604ኛ ኮር የተደመሰሰበት የሽረ ጦርነት የጎበኙ ታዋቂ የአገሪቱ አርቲስቶች ያዩት
ነገር ከዚህ በፊት ከሰሙትና ካነበቡት የተለየ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ብዙ ውጣ ውረድና ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘ ድል አሁን
በኢሕአዴግ ሹማምንቶች እየረከሰ በመሆኑ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠየቁ፡፡;
ምን ማለት ነው ከአውራ ሹማሙንቶች ጋር እየተንደላቀቁ ስለ ሹማሙንት ማውራት? ሌላ የኢህዴግ ልደትን ከእነእርሱ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ያላከበሩ ሹማምንቶችን ማለት ይሆን? መንገድ ላይ ተቀላቅለው ሹማምንት የሆኑትን ነውን? በትጥቅ
ትግል ያለነበሩ አሁን ሹማምነት የሆኑትን ማለት ይሆን? በሀቀኛ የጭቆና
ስሜት ተነስተው በየበረሃው የተሰዉትን ታጋዮች ዓላማ ወርውረው
ጥለው ዘመናዊ ጨቋኝ የሆኑትን ይሆን? በሞት ሽረት ትግል ወቅት በሴት ታጋዮች
ጀርባ ጥይት ሲከለሉ ነበሩ የተባሉት ይሆን? እንማንን
ይሆኑ እነዚህ ሹማሙንቶች?
ጎናቸው የተቀመጡትና የቆመት እየተሸከረከሩ አብረዋቸው ፎቶ የሚነሱት ሹማምንቶች የኢህዴግ ሹማምነቶች አይደሉም ይሆን?! ወይስ እርምጃ ወሳጆቹ
ጋር ሆነው ነው የእርምጃ
ይወሰድ ጥያቄ የሚያነሱት?!
እረከሰ ማለት ምን ማለት ነው?!
ምክንያት እየፈጠሩ በህዝብ ገንዘብ መጨፈር፣ መዝናናት፣ ከሆቴል ሆቴል
እያማረጡ መጠጣት መብላት ነው? ስልጣንን መከታ በማድረግ
የህዝብ ገንዘብ መዝረፍ ነው? ምክንያት እየፈጠሩ በቡድን እየተከፋፈሉ የግዙፍ ካንፓኒ ባለቤት መሆን ነው? በሀገሪቱ ከሚገኙ ታላላቅ
ኩባንያዎች ውስጥ ባለድርሻ መሆን ነው? ደሃውን ህዝብ ከቡና በጀበና እያፈላህ ከምትሸጠው የመንግስት ግብር ክፈል በሎ
በማስጨነቅ በካንፓኒያአቸው የንግድ እንቅስቃሴ ለመንግስት ግብር መግባት
ያለበትን በቢሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ ሎሌዎቻቸአቸውን አላያችሁም
ማለት ነው በማለት አይን በማሰጨፈን በነጻ በመነገድ በሀበት መንበሽበሽ
ነው?!
ዘገባውን እያነበብኩ በውስጤ የተፈጠሩትን እንዚህ ጥያቄዎችን አዝዬ ወደ ታች
ስወርድ እንዲህ የሚል ጹህፍ አነበብኩ፡፡
‹‹ይኼን የመሰለ ከባድ መስዋዕትነት የተከፈለበት መሆኑን እስከዛሬ አላውቅም ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን የታጋዮች ዓላማ የሚያረክስ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ እናንተን የማይመስሉ ባለሥልጣናት ሾማችሁብናል፡፡ ሕዝቡን ከታች እስከ ላይ እያማረሩ ነው፡፡ ትናንት የደማችሁለት ቅዱስ ዓላማ ዛሬ እየተበላሸና እየረከሰ ነው፡፡ አርሟቸው፡፡ እኛም ጦር ይዘን ከጎናችሁ እንቆማለን፤›› የሚለው ንግግራቸው በጉብኝቱ ተሳታፊዎች ከፍተኛ ጭብጨባ የታጀበ ነበር፡፡ ‹‹እናንተም ላሳያችሁ ፍቅርና ትህትናችሁ እግዚአብሔር ዋጋችሁን ይክፈላችሁ፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ይህ አንቀጽ ቀደም ብዬ ያነሳዋቸውን ጥያቄዎችን የመለሰልኝ ቢሆንም ሌላ ጥያቄ እንዳነሳና አቤት ውሸት!!
አቤት ቅጥፈት! አቤት ጥምጠማ! አቤት ማሸርገድ! አቤት ህሊና! ብዬ ጨንቅላቴን እንድይዝ ነው ያደረገኝ፡፡ እስቲ አርቲስቶቹ
የሰነዘሩትን የመፈክር ሀረጎችን እየመዘዝን እንገማገም፡፡
ይህን
የመሰለ ከባድ መስዋትነት የተከፈለበት መሆኑን እስከ ዛሬ አላውቅም ነበር!
ለአለፉት 23 ዓመታት ኢህአዴግ ደርግን ያንበረከክንበት ቀን ግንቦት 20 ብሶት የወለደው…. ለህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል
ሲል ይህ አስተያየት ሰጪ የጦርነቱን ፊልም በቴሌቪዥን ወይ በቪድዮ ወይ በሬድዮ አላየሁም ወይ አልሰማሁም እያለ ነው ማለት ነው፡፡
ወይ ደግሞ እየጠመጠመ ነው፡፡
እናንተን
የማይመስሉ ባለሥልጣናት ሾማችሁብናል!!
በዚህ ሀረግ መስዋዕቱን አርካሾቹ ቢያንስ
ቢያንስ አበረዋቸው ያሉት ሹማምንቶች አለመሆናቸውንና ታግለው ያልመጡ
ሹማምንቶች መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ እንደ እናንተ ምርጥ መሪ ያልሆኑ፣ እንደ እናንተ በስማቸው ግዙፍ ካንፓኒ የሌላቸው፣ እንደ እናንተ ዲሞክራሲያዊ መብት የሚያከብሩ፣ እንደ
እናንተ የማያሳድዱ፣ እንደ እናንተ ድንጋይ ለያዘ ጥይት የማይተኩሱ፣ እንደ እናንተ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ የሌላቸው ፣እንደ እናንተ ስንት ቁርጠኛ ታጋይ መስዋትነት የከፈለበት ድል የገባቸው፣ እንደ እናንተ
የሴቶችን መብት የሚያከብሩ፣ እንደ እናንተ የማያዋክቡ፣ እንደ እናንተ
በነፃነት በህዝብ መሃል የሚሄዱ፣ እንደ እናንተ በሆድ ሰው የማይደልሉ፣ እንደ እናንተ ሴራ ያማይጠነስሱ የማያስፈራሩ፣ እንደ እናንተ ዜጋውን የማያሰቃዩ ወዘተ….አይደሉም የሚሉ ይመስላሉ አርቲስቶቻችን፡፡
ይሁንና በኢህአዴግ መዋቅር ውስጥ እነሱን ያልመሰለ ከእነእርሱ ጋር የሚቀጥል ስላለመሆኑ ፀሃይ የሞቀው እውነታ መሆኑን ያላወቁ በመምሰል ሲጠመጠሙ
ያሳየናል፡፡ ኢህአዴጎች አንድ መጽሀፍ እንደ አነበቡ ሰዎች አይነት አነድ
መሆናቸውን ነብሳቸውን ይማረውና የቀድሞ ጠቅላይ
ሚኒስትርና የኢአህዴግ ሊቃመንበር በአንድ ወቅት በፓርላማ ላይ ነገርውን ነበር፡፡
ሕዝቡን ከታች እስከ ላይ እያማረሩ ነው፡፡ ትናንት የደማችሁለት ቅዱስ ዓላማ ዛሬ እየተበላሸና እየረከሰ ነው፡፡ አርሟቸው፡፡ እኛም ጦር ይዘን ከጎናችሁ እንቆማለን፤››
በዚህ ዓረፍተ ነገር ደግሞ
የእዝቡ ምሬት ውስጣቸው የገባ
መሆኑን ሊነግሩን ይሞክራሉ፡፡ ድንቄም ለህዝብ ተቆርቃሪ፡፡
የያዛችሁትን የኪነጥበብ ጦር የህዝብን ምሬት ለማሰማት ስንታችሁ ናችሁ የተጠቀማችሁበት? ለህዝብ ከያኒ የህዝቡን ምሬት መግለጫ ዋናው መሳሪያ
በእጃችሁ የያዛችሁት ኪነጥበብ አልነበር እንዴ? እናንተ ስትዝናኑ ህዝቡ ጉልበቱን
ታቅፎ በባዶ ሆዱ የሰው ያለህ ሲል ቢያንስ ቢያነስ
በኪነታችሁ ስትጮሁ አላየንም ፣ የህዝብ መሆናችሁን ከማሳየት ይልቅ ፤ አልሰማንም አላየንም ብላችሁ
ስለመንግስተ ሰማያት ስትሰብኩን የቄሱን ሥራ እናንተ ስትሰሩ
ያጢሳችሁን፣ ለአጭሩ ዕድሚያችሁ አይኔን ግንባር
ያርገው ማላታችሁ አልበዛም ቢላችሁ ህዝቡ መልስ ይኖራችሁ ይሆን?
ጦር ይዛችሁ ላለመቆማችሁ ምን ያህል እርግጠኞች
ናችሁ? እጃችሁ ላይ የግድ ጦር ጨብጣችሁ ማየት ህዝቡ
ከእናንተ የሚጠብቅ ይመስላችሁ ይሆን? የጨበጣችሁት ርህራሄ የሌለው የማይታይ ጦር ስለመሆኑ ምን ዋስትና
አላችሁ? የሠራዊት መር አርቲስቶች አይደለንም የማለት
ሞራሉ እውን አላችሁ?! እስቲ የህዝቡን ምሬት ያሳያችሁበት አንዲት ጠብታ የጥበብ ስራችሁን እንሆ በማለት ማስረጃ ጥቀሱ፡፡ የተመለመላችሁበት መስፈርት የህዝብን ምሬት ለመንግሰት በማስተጋባታችሁ ይሆን?! የህዝብን ምሬት የሚያስተጋቡ የት ነው ያሉት?
‹‹እናንተም
ላሳያችሁ ፍቅርና ትህትናችሁ እግዚአብሔር ዋጋችሁን ይክፈላችሁ፤››
ይህ ዓረፍተ
ነገር እንዲህ የሚል ቶን ያለው ይመስለኛል፡፡እናንተ በመኪና እያንሸራሸራችሁን
ከእናንተ እኩል እንድንመስል በማድረጋችሁ፣ ዘና እንድንል ስላደረጋችሁን፣ ሆቴሎች ስላሳያችሁን፣ አጠገባችሁ ፎተ ስለተነሳን፣ እናንተ የተታኮሳችሁበት ታንክ ላይ ፊጢጥ ብለን ስለአቅራራን፣ እንደ ጓዳችሁ አቅርባችሁ አብዮታዊ መመሪያ ስለሰጣችሁን፣ ቢሮአችሁ ሰተት ብለን እንድንገባ አጋጣሚውን
ስለፈጠራችሁልን፣ የሀገሪቷ ቁንጮ ሹማምንቶችን ስልክ በቀላሉ ስለአገኘን፣
የሆነ ፕሮጀክት ይዛችሁ ኑ እናጸድቅላችሁለን ስላላችሁን፣ የበለጠ በጋራ የምንሰራበትን ሁኔታ የያዛችሁትን
ሥልጣን መከታ በማድረግ እንደምታመቻቹልን ቃል ስለገባችሁልን ወዘተ… እግዝሐብሔር ዋጋችሁን ይክፈላቸሁ
እያላቸሁ ይመስለናል ብንልስ ሰይጣናዊ ሀሳብ አሰብን እንባል
ይሆን!?
ህብረ-ቃል፣
ሰሙ፣ ወርቁ እያልን የዘገባውን ይዘት በእኛ አይን ብንፈታው ክፉ አሳቢ! ቡዳ! ምን አለ ብንሞዳሞድ!? ምን አለ በተገኘው አጋጣሚ
የድርሻችንን ይዘን አገራችንን ወደ መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር ብንቅላቅላት!? ምን አለ በተዘዋዋሪ መንገድ በቀኝ አዙር
ለአገራቸው የሰሩ ተብለን ሽልማት ቢጤ በተመቻቸ መድረክ
ቢሰጠንና ከፍ ከፍ ብንደረግ! ምን አለ በኛ ከፍ ከፍ ማለትና በእኛ
መሸለም አንሞዳሞድም ብለው በችጋር የሚቆራሞቱ እነ በዓሉ ግርማ፣ ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህን ወዘተ.. የሚያክሉ የጥበብ ፈርጦች ናቸው፣
ክላሲክ ሥራ ሰርተዋል ሳይባሉ እንደተገለሉ ማለፋቸው ትርፍ ያላገኙበት ኪሳራ
መሆኑ ያልገባቸውን የሞያ ታላላቆቻንን አንጎል ብናደርጋቸው!?
ደግሞ! ደሞ.. ደሞ! .. ከጎናችን የተሰለፉ በጸሐፊ እና በነፃ
ጋዜጠኝነት ስም የሚጫወቱ ትርፍራፊ የሚለቃቅሙ አንድ አንድ ጋዜጠኛ ተብዬዎቻችንስ!? በቀኝ አዙር እጅ መንሻ የሚሰጣቸው፣ ወደ መካከለኛ
ባለሀብትነት ለመቀላቀል የህዝብ ምሬት ብዕራችን አይጽፍልንም! አያዋጣም! አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ጹህፍ እየጻፍን፣ እያስጻፍን አብዮቱ ግቡን እንዲመታ ዘና ብለን ማኪያቶአችንን እየጠጣን የድርሻችንን እናበረክታለን
የሚሉትስ?! ለምን እኛ ብቻ ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ እውነተ ነው በዚህ
እንስማማለን በቀጣይ ግለ ሂሴን አወርዳለው፡፡
ሲጠቃለል!
የተወሰኑ አርቲስቶቻችን ከመሸ የደርግ ዘመን አብዮታዊ ኪነትን ሊያመጡ ሲራወጡ እየታዘብን ነው፡፡ አንድ አንድ ጊዜ በቴሌቪዠን
መስኮት እነዚህን አርቲስቶችን ስመለከት በደርግ ዘመን ከአብዮታዊ
መሪያችን ጋር ወደፊት በማለት የፕሮፓጋንዳ ዘፈን ሲዘፍኑ የነበሩትን አስተኳሽ እርካሽ ተወዳጅ የኪነጥበብ ሰዎችን የስታውሱኛል፡፡
የሚገርመው አንዳንዱ አሁንም ማሊያቸውን ቀይረው ልማታዊ መንግስታችን፤
ልማታዊ መሪያችን ሲሉ እንደ ቅዠት
ሁሉ ይታዩናል፡፡ በደርግ ዘመን በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በውትድርና ውሰጥ ተሳትፈው የአንባገነኑን ደርግ
መንግሰትን እድሜ ለማራዘም አንድ ጥይት እሰከሚቀር ድረስ በሚል ቀመር የበኩላቸውን አስተዋፆ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በአርቲስት
ስም በሞቀበት የማድመቅ የረጅም ጊዜ ልምድ አለን በማለት የለመዱትን ወደፊት በሉለት! ከቀድሞ መንግስት ኢኮነሚያዊ ይዞታ በተሻለ መልኩ
ሆነው በግል መኪናቸው እየተሸከረከሩ በተሸከርካሪ ወንበር ላይ እየተንደላቀቁ በትርፍ ሰዓታቸው አብዮታዊ ግዴታቸውን ሲወጡ ሳንፈልግ
በግድ በየቤታችን ቤተሌቪዥን መስኮት አናያቸዋለን፡፡ የሚገርመው ጉዳይ
እየሰሩት ያለው ነገር ከህዝብ ያጋጨኛል ብለው ለጥቂት ሰከንድም የሚያሰቡ አይመስሉም፡፡ አርቲስት ነኝ የህዝብ ሀብት ነኝ፣ ነን እያሉ እነ ህዝቡ የሰሩትን የኪነጥበብ ሥራ በማድነቅ፣ በማክበር ከእለት ጉርሱ እየቀነስ
ከፍሏቸው እደጉ ተመንደጉ በማለት ከምንምና ከባዶ እርሱ እየተራበ ወደ ባለሃብትነት ጎራ ሲቀላቅለቀቸው ይህንን ምሲከን ህዝብ ቁልቁል በመመልከት በምን ታመጣለህ መንፈስ ሲፎክሩ፣
አመራር ሲቀበሉ፣ ከህዝብ ልብ ውስጥ ብንወጣም በቀኝ አዙር የህዝቡን ገንዘብና ሀብት እርግጫችን እስከ አለ ድረስ እኛም አለን ሲሉ፣ ከህዝብ ያልሆነ የህዝቡን ችግርና ብሶት ያላሳየ አርርቲስት ነኝ
ባይ የኪነ ጥበብ ባለሞያ ሳይሆን ሠራዊት መር ቡድን ነው፡፡ እርግጥ
ነው አንድ የጋዜጠኛ ማህበር ሊቀመንበር በኢትዮጵያ ውስጥ በጋዜጠኞች
ላይ ስለሚደርሰባቸው እስርና ወከባ ሲጠየቁ ለጠያቂው ጋዜጠኛ እኔ ባክህ ቦሌ ላይ ማኪያቶዬን እየጠጣው ቺኬን(ቆነጃጅት
ሴቶችን ማለቱ ነው) ነው ማየት የምፈልገው ብለው እንዳሉት እነዚህም እንደዚህ አይነት የህይወት ፍልስፍና የላቸውም ብለን ለማለት
ሥራ ነገራቸውን ማስተዋል በቂ ነው፡፡
ሰው በላው ኢዲያሚን ዳዳ፣የሰው ልጅን በቁሙ እያሰለፈ በእሳት የሚያቃጥለው
በመርዝ የሚፈጀውም ሂትለር ህዝቡ፣ ህዝባችን እያሉ የሚፈጁት ህዝብ ፣ ህዝብ አይደለምን እንዴ ? የሚል ጥያቄ ሲነሳ መልሳቸው ለህዝብ
ነው የምንኖረው፣ የምንሰራው በማለት ከአፋቸው የሚወጣ ሠርክ የምንሰማው መፈክራቸው መሆኑን ከታሪክ ስንረዳ በእርግጥም ለህዝብ ማለት
ምን ማለት ነው ብለን ብንጠየቅ ትክክል ነው፡፡
ምናልባት ህዝብ የሚለው ቃል ህዝብ
የሚጨቁነውም ለህዝብ የቆመውም የሚጠቀምበት ስለሆነ ህዝብ ማለት መንግሰት ነው( የማይሰራ፤ ያረጀና ያፈጀ አይንህን ያዝ ላሞኝህ
ፍልስፍና)፣ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ትንታኔ፣ ትርጉም፣ ጽንሰ ሀሳብ በማለት
አርቲስቶቻችንን የባሰ ግራ ሳናጋባ በዚህ ጸሓፊ እምነት ህዝብ ማለት ጎረቤታቸችን የሚበሉ የሚጠጡት ያጡ
ወገኖቻችን፣ መንገድ ላይ በላስቲክ ቤት ልጆቻቸውን ሰብስበው በልመና ያገኟትን እንጀራ ለመብላት ድንጋይ ጎልተው ወጥ የሚወጠውጡ፣
ጀርባቸው እስኪጎብጥ በደከመ አቅማቸው ቅጠል ተሸክመው ቁና ቁና የሚተነፍሱ፣
ሆዳቸው ተጣብቆ አውላላ ሜዳ ላይ ተዘርረው ማን ነህ ያልተባሉ
ወገኖች፣ ከገንዳ ላይ ከውሻ አጥንት እየተናጠቁ የሚግጡ፣ በአስተዳደር በደል የህይወታቸው አቅጣጫ ተቀይሮ ከብርሃን በፈጠነ ሁኔታ
ስራ አልባ የሆኑ ፣ቤት አልባ የሆኑ፣ ንብረት አላባ የሆኑ፣ በአመለካከታቸው ምክንያት የተሰደዱ፣ የታሰሩ ፣ የተገለሉ፣ ቤተሰባቸው
የተበተነ፣ወዘተ….. ናቸው ብንል የህዝብ ትርጉምን አጣመሃል እነደማንባል ተሰፋ እያደረግን ነው፡፡ ስለ እነዚህ የሚሰራ ነገር አይኖር ይሆን!? ይሄ ለኪነጥበብ ባለሞያው ውሃ የማይቋጥር ጭብጥ(theme)
ሆኖ ይሆን! ወይስ ይሄ ወቅታዊ ጉዳይ ስላልሆነ!? ወይሰ በእሳት
ጫዋታ እናዳይሆን! የዚህ ጹህፍ ጸሐፊ መልዕክት ግን በምንም በማንኛውም
መንገድ! በየትኛውም ሂሳብ ከያኒ ከህዝብ ከተለየና ሹማምነት ልሁን ካለ ይሀ አርቲስት ሳይሆን ገዢ ነው! ገዚዎች ደግሞ ሁሌ አይኖሩም ህዘብ ግን ለዘላለም ይኖራል፡፡ አሁን አገር
ይያዝልኝ! ያዙኝ ልቀቁኝ የሚል( በአንድ ናይት ክለብ ሲዘፍን መዳከሙን አይተው ደጉ ሰውዬ ሚሊየን ብር እጅ መንሻ ሰጥተው ነፍሱን እንዲዘራ ያደረጉት አርቲስት፡፡) በደርግ ዘመንም እንደዚሁ
ሀገሬን!... በማለት በመፎከሩ የምናውቀው አርቲሰት በሰባዎቹ አጋማሽ ላይ በአንድ መጽሔት ላይ የጠቀሳትን ጥቅስ እኔም ልጥቀስና ጹሑፌን ላጠናቅቅ፡፡ «አርቲስት በህዝብ
መዳፍ ላይ እንዳለ እንቁላል ነው»፡፡
በዝራው አሻግሬ