ሰኞ 20 ኦክቶበር 2014

የኢቲቪ/ኢብኮ ፀሐፊና የፖለቲካ ተንታኝ!


የኢቲቪ/ኢብኮ ፀሐፊና የፖለቲካ ተንታኝ!

   
ድንገት ጋደኛዬ ከእንቅልፍ ቀሰቀሰኝና ከዚህ ቀደም ጋዜጠኞን በቴሌቪዥን ሲሳደብ የነበረው ካድሬ አሁንም እያወራ ነው ተነስተህ ተከታተለው አለችኝ፡፡  ከእንቅልፌ ተነስቼ ኢቲቪን(የአሁኑ ኢብኮን)መከታተል ጀመርኩ፡፡ የህትመት ዳሰሳ ታደሰ ሚዛን በተባለ የዝግጅቱ አቅራቢ አማካኝነት እየቀረበ ያለ ቃለምልልስ ነው፡፡ በቴሌቪዥን ላይ ቃለመጠይቅ የሚደረግለትን ሰው ተመለከትኩት፡፡ ለጋደኛዬ መለስኩላት ይህ ሰው ይፋዊ ካድሬ አይደለም ግን እንዳልሽው የካድሬዎችን ሥራ አፈፍ አድርጎ በመውሰድ በገለልተኘ ስም ከእኔ ወዲያ ለአሳር የሚል ግለሰብ ነው፡፡ አቶ ዘሪሁን ይባላል፡፡ ከዛሬ ሰባት ዓመት
በፊት የሞተች ኢፍትን የምትባል ጋዜጣ አዘጋጅ የነበሩ የዛሚ ሬድዮ ባለቤት እና የመንግስት ተቃዋሚዎችን በሬድዮ ጣቢያቸው የሚያወገዙ እና ለጊዜው አሁን እዚህ ላይ ልገልጽ ያልፈለኩትን የእሳቸውን ተግባር የፈጸሙ ሰው ናቸው ብዬ ኢቲቪ ፀሐፊና የፖለቲካ  ተንታኝ ስለአላቸው ሰው መረጃ ሰጠዋት፡፡
 
እኔ ባለኝ መረጃ እኝህ ግለሰብ የፍልስፍና መምህር የነበሩ ኢህአዴግ ከአባረራቸው 42 የዩኒቭርስቲ መምህራን መካከል የነበሩ በዚህ ምክንያት ውጭ አገር ተሰድደው ማሊያቸውን ቀይረው አገራቸው የተመለሱ መሆኑን እንጂ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ያላቸው የፖለቲካ  ተንታኝ አለመሆናቸውን ነው፡፡  ኢቲቪ (የአሁኑ ኢብኮ) ለእርሱ የሚመቹትን የአንድ ወገን ታሪክ ነጋሪዎችን በቴሌቪዥን እያቀረበ ጉልቻ በመለዋወጥ በልማታዊ ፕሮፓጋንዳው ያደነቁርናል፡፡
   
ኢቲቪ የተለያያ ማዕረግ እየሰጣቸው የሚያቀርባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የሚዘውሩት ወሬና ኢቲቪ የሚሰራው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጉንጭ አልፋ ልፈፋ መሆኑን በዳሰሳ ለማየት የሚችገር አይደለም፡፡ በቀላሉ አንድ ምሳሌ ብንጠቅስ እንኳን፤ የኢትዮጵያ የግል ጋዜጠኞች የጋዜጠኝነት መርህን አይከተሉም፣ የአንድ ወገን ወሬ ነው የሚያወሩት፣ ስለልማት አይዘግቡም እያሉ እያወሩ እነእርሱ የጋዜጠኝነት መርህ ቀልድ እንደሆነባቸው አስረግጠው የሚያሳዩን፤ በሆነ ጉዳይ ላይ የሚያቀርቡት ዘገባ ጭልምተኝነት የተሞላ የገዢውን ፓርቲ አስተሳሰብ ብቻ የሚያንጸባርቅ፣ አማራጭ ሀሳብ የሚያቀርብ ምሁር ወይም ግለሰብ
የማያቀርቡ ድንገት በአጋጣሚ እንካን ከገዢው ፓርቲ ተቃራኒ የሆነ ሀሳብ የሚያራምድ ሀሳብ ያለው ያቀረቡ ከሆነ ቆራርጠው ለእነእርሱ የሚያግዝ ሀሳብ ለማቅረብ ስቲድዮ ውስጥ ሲቸገሩ የህዝቡን ገንዘብ በየወሩ እየቆጠሩ ገዳዳ መረጃ ለህዝቡ የሚሰጡ ጋዜጠኞች ያአየንበት ነው፡፡ ተሳስተው እንካን የመንግስት ወይም የገዛዢው ፓርቲን ስህተትና  ችግር በተገቢው ሁኔታ በማሳየት ገለልተኝነት የሚባል ነገር እንደሚያውቁ ድንገት ያሳዩን ጊዜ ትዝ አይለንም፣ እየሰበሰቡ የሚያመጧቸው ተንታኝ ወይም ሙህር የሚባሉትም የኛ ሰው ነው በሚል ስለት የሚቀርቡ፣ በድፍረት የእነእርሱን ዜማ ቋንቋ እየቀየረ እየቀለጸ
የአንድ ወገን ወሬ የሚያወራ ተራጋሚ እንጂ በገለልተኛ ስሜት ወይም አስተሳሰብ በአርቆ አስተዋይነት  ሚዛናዊ አስተያያት የማይሰጥ፣ አይኔን ግንባር ያርግው ብሎ የሚቀደውን ወሬ ህዝቡ ይታዘበኛል የማይል(በመሰረቱ አንደኛው የኢቲቪ መስፈርት በሚወራው የፈጠራ ድርሰት ስለህዝብ ግድ የሌለው አይኑን አፍጥቶ የሚናገር፣በዚህ መንግስት በአንደም ይሁን በሌላ መንገድ ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ የተጠቀመ፣ለዛሬ የሚኖር፣ አፈቀላጤ እየመረጠ አይደለም  ለማለት ያስቸግራል፡፡) ደፋር የሆነን ሰው ነው፡፡ 
     
አንድ የግል ጋዜጣ አዘጋጅ የሆነ በተወሰነ የምንቀራረብ በኢቲቪ ለቃለመጠየቅ የቀረበ ጋዜጠኛ ሲያጨውተኝ በኢዚአ አማካኝነት ለቃለምልልስ እንደተጋበዘና ቃለምልልስ  ባደረገበት ጉዳይ ላይ ኢዚአ ያደረገውን ዘዴ ሲናገር እኛን  ስለ ግል ፕሬሱ አስተያየት እንድንሰጥ ጠየቁን፡፡ ሀሳባችን ስነዘርን እኛን ያናገሩን  ወይም ያቀረብነውን  ሀሳብ  ፊት ለፊት ባልተገናኘንበት ሁኔታ ወይም በኛ አስተያየት ላይ የተሰጠውን ምላሽ እኛ  ምላሽ  ሳንሰጥበት የእነእርሱ ሰዎች ወይም እነእርሱ የሚፈልጉትን የሚያንጸባርቁ ሰዎችን መልስ በማሰጠት እነእርሱ የሚሰጡት ትንታኔ ወይም ምላሸ ትክክል  በሚያስመስል
ድምዳሜ ፕሮግራም  ሰርተው  መዝጋታቸው  በጣም አስደምሞኛል ብሎኛል፡፡
ስለ ግሉፕሬስ ወገንተኝነት ሲያወሩ እነ አዲስ ዘመን፣አብዮታዊ ዲሞክራሲና መሰል የመንግስትና የፓርቲ የህትመት ውጤቶች ገዢው መንግስት ወይም  ሞት የሚል ዓላማ በማራመድ ተቃራኒ ሀሳብ የሚያራምድ አካል ወይም ግለሰብ ለሚዛናዊነት ማቀረብ ሞታቸው ነው፤ ድንገት አስገዳጅ ሁኔታ ተፈጥሮ ወይም ለሚፈልጉት ዓላማ አቀረቡ እንኳን ቢባል መቆራረጡን፣ በእጅ አዙር በብዕር ስም እዛው የህትመት ውጤት ላይ አሰተሳሰቡን ለመምታት አፈርድሜ መብላቱ የእጃቸው ነው፡፡
   
ታዲያ እንዴት ነው አይኑ ላይ የቆመበትን ጉድፍ ሳያይ የሰው ጉድፍ አሳያለው  የሚለው? እኔ ማነኝ አየተዘጋ ለአለው ኢቲቪ አይገባውም?!
 
እስቲ የኢቲቪ የፀሐፊና ተንታኙ ትንተና ላይ በወፍ  በረር እንቃኝ፡፡ እኝህ ተንታኝ ከዚህ የህትመት ሚዲያ በፊት በነበረው ዝግጅት ላይ ስድብ ቀረሽ ትንተና በአደባባይ ሲያደርጉ እንደነበረ ጋደኛዬ ገርሟት ስትከታተለው እንደነበረ ገልጻልኛለች፡፡ የግል ጋዜጣ ጸሐፊዎች ጥቅማቸው የተነካባቸው፣አርቲስቶች ወዘተናቸው እያሉ ሲፈርጁ እንደነበረም ሰምተናል፡፡ እርሶስ ጥቅም ስለአገኙ አይደል በድፍረትና በህዝብ ንቀት ውለታ የሚመልሱት ብለን በእንጠይቅ ዝርዝሩን ማሰቀመጥ ይጠበቅብን ይሆን? ለጋዜጠኝነት የሚቀርበውስ አርቲስት ነው የፍልስፍና ተማሪ? ብሎ በጥቂቱ ቀላል መከራከሪያ ሀሰብ ማቅርብ
ይቻላል፡፡ 
 
በዚህ እኔ በተከታተልኩት ትንተና ላይ አንዴ በእርሳቸው ሬድዮ ላይ እኔ ደጋግሜ የምናገር የነበረውን ሀሳብ እንዳነሳ ዳዳኝ፡፡ «በአገኘነውን የመገናኛ  ብዙሃን ላይ ዝም ብለን ያገኘነውን መተንፈስ ከእኛ እጥፍ በጉዳዩ ላይ እውቀት ያላቸው ባለሞያዎች ፈልገውም ይሁን ሳይፈልጉ በአጋጣሚ ሳይወዱ በግዳቸው እያዳመጡን ስለሚሆን መድረኩን ይዘነዋል ብለን በድፍረት አንናገር እናውቃለን የምንላትንት ኢምንት ነገር እንደ አዋቂ አንናገር» እል  ነበር፡፡ ግለሰቡ በምን ታመጣላችሁ የሚያወሩትን ትንተና በመልክ በመልኩ እየደረደረ ሊያሳያቸው የሚችሉ ብቁ ተመልካች ያለ ሁሉ አይመስልም ሲያወሩ፡፡
አንዳንዴ ከእኔ ወዲያ አገር ወዳድ የሚል ሁሉ ይመስላሉ፡፡ አነጋገሩ እርግጥ ነው በራሳቸው ሬድዮ ጣቢያ በባለቤታቸው ሲጋበዙ ሲያወሩም ድምፀታቸውና አወራራቸው የደርግ ዘመን የአስቸኳይ  ጊዜ አዋጅ አንባቢ ድምጽን ያስታውሱናል፡፡
   
ጋዜጠኛ ማለት የልማት ጥያቄን የሚያነሳና ስለ ብሄር ብሄረሰብ የሚዘምር ነው እያሉ ሊሰብኩን ሲዳዱ አይተናል፡፡ የጋዜጣ አሳታሚዎች ሲከሰሱ እንዴት ጋዜጠኞች ይሰደዳሉ እያሉ በፍልስፍና ተገኘች ያሉት ሀሳብ ለኢቲቪ ሲያቀርቡ አይተናል፡፡ ለምንስ ህጉን  ተከሰው አይፈትሹትም እያሉ የሊቅ ምክር ለጋዜጠኞቻችን ይለግሳሉ፡፡(ያልተነካ ግልግል ያውቃል እንደሚሉት)እርግጥ ነው ጋዜጠኞቹ በአሁኑ ኬዝ አልተከሰሱም፡፡ ቀጥሎ አይከሰሱም ማለትም አይደለም! ግን አንድ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ አንደኛው ጋዜጠኞቹ የሚሰሩበት ድርጅት አሰተዳዳሪዎች ሲከሰሱ የህትመት ውጤቱ ሲታገድ በምን ላይ ይስሩ?!
በመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ህግ ለህትመት ውጤቶች የህትመት ውጤቱ ዋና አዘጋጅ ዋና የህግ ተጠያቂ ነው እየተባለ ተነጥሎ የህትመት ውጤት ባለቤቶችን መክሰስ ምን ማለት ነው? ህትመት ውጤቶቹ ባለቤቶች ውስጥ ጋዜጠኞች የሉም እንዴ? (ለምሳሌ የሎሚ ጋዜጣ ባለቤት ግዛው ታዬን ብናነሳ)ለምን ህጉን አይፈትሹም ማለት ምን ማለት ነው? ስንቴ ይፈተሸ? እነዚህ ሰዎች የግድ በራሳቸው ህጉን መፈተሸ አይጠበቅባቸውም? ብልህ ሰው በሞኝ ይማራል የሚባለው ፍልስፍና ላይ አትኖር ይሆን? ወይስ አላስፈላጊ መስዋትነት መክፈል ነበረባቸው!?
 
ዝም ብለን ስናስተውል ፀሐፊና የፖለቲካ ተንታኝ የተባሉት ሰው አንደ ገለልተኛ ሰው እንዳንዴ ደግሞ እንደ ወሳኝ የመንግስት አካል እየሆኑ ነው ትንታኔ የሚሠጡት ቃለመጠይቅ አድራጊው ታደሰ ሚዛን የህትመት መገናኛ ብዙሃን ፍቃድ ተሰጥቷቸው ወደ ስራ አልገቡም ይሄ ነገር አሁን ከተወሰደው እርምጃ ጋር የተያያዘ ይሆን? ከዚህ በተጨማሪም ከታገዱት መጽሄቶች ጋር መተካካት አይሰሩም ይላሉ ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ ተንታኙ መልስ ሲሰጡ እነዚህ ፍቃድ የተሰጣቸው 8 ወር በፊት፤ ክስ የተመሰረተው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በማለት ምክንያቱ ይሄ አይመስለኝም በማለት ገለልተኛ የሚመስልና እንደገና ስለ
አመለከቱት የህትመት ውጤቶች ላይ መረጃ ከመንግሰት እንዳላቸው በሚያሳብቅ ሁኔታ ይመልሳሉ፡፡ በተጨማሪም የመንግስት ካድሬዎች እነእርሱንና ሥራዎቻቸውን የሚቃወሙት ግለሰቦችና አካላቶችን የሚያወግዙበት የዘውትር የማይለወጥ እጅ እጅ የሚል ቋንቋቸው የሆነውን ጥቅማቸው የተነካባቸው ወይም የጎደለባቸው ሰዎች ናቸው በማለት እኚህው ተንታኝ የካድሬ አጋሮቻቸው ቋንቋ እንኳን ለመቀየር አለመቻላቸውን ተመልክተናል፡፡

ሲጠቃለል!
 
ኢቲቪ በእርግጥ መደበኛው ሥራው ፕሮፓጋንዳ መሥራት የፈጠራ ታሪክ ማቀናበር የሰርክ ሥራው እስኪመስል የተጋ ቢሆንም፤ በተቻለ መጠን ጣቱን ሰው ላይ  ከሚቀስር እራሱን በስም  ከመቀየር የዘለለ የጋዜጠኝነትን ሥራ በመሠራት ሚዛናዊ በመሆን፣ ለህግና ለሞራል  በመገዛት  እንዲለውጥ እንመክራልን፡፡ አለበለዚያ  እሱና የአሱ አጋሮች ብቻ የሚያዩት የቴሌቪዝን  ጣቢያ ሆኖ ያዝ ለቀቅ የሚደርገው ተመልካቹ ህዝብ ሙሉ በሙሉ ጥርቅም አድርጎ እንዳይዘጋው ለራሱ ሲል መሥራት ያለብት ይመስለኛል(ለማመሳከር እንዲረዳ  በቀላሉ በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉትን ቤቶች ጣራ ላይ  የተተከሉትን ዲሽ ማየት ይችላል፡፡) ኢቲቪ
ተንታኞችና ምሁራን ተብዬዎች ወይም ግለሰቦች አብሮአችው የሚኖረውን ህዝብ የሚያወቀውን እውነት በመሸፈን አፈቀላጤናታችሁን በመጠቀም ለጊዜው ያገኛችሁትን ጥቅም መሰረት በማድረግ በበላችሁበት ባትጮሁ፣ ተመልካቹን ባታሰለቹ፣ከእውነት ጋር  ባትጋጬ ህዝቡን ባታስከፉ፣ ነገን ብታስቡ ጥሩ  ነው፡፡
    
             በዝራው አሻግሬ
Top of Form

Bottom of Form
Top of Form
   
Bottom of Form
Top of Form

Bottom of Form
Top of Form
Bottom of Form